የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 የ2010 የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳሉ። ቅዳሜ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም መከላከያ ከሙገር ሲሚንቶ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከ30፤ እንዲሁም አዲስ አበባ ፖሊስ ከጣና ባህርዳር ከረፋዱ አራት ሰዓት ይጫወታሉ። እሁድ በክልል ከተማ ሮቤ ላይ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከፌዴራል ማረሚያ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከ30 የሚጫወቱ ይሆናል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሰባት ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር ነው። የ2010 የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግንቦት 20 ቀን 2010 በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም የሚካሄዱ ይሆናል። የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ከጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ከጠዋቱ 2 ፡30 የሚካሄድ ሲሆን ፌዴራል ማረሚያ ከኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ከረፋዱ 4፡30 ላይ ይጫወታሉ። በኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አራት ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል። በሌላ በኩል አራት ቡድኖች በሚሳተፉበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ-ግብር ከነገ በስቲያ ባህርዳር ላይ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከወልቂጤ ከተማ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።