ቀጥታ፡

አርበኛና ገጣሚው ሰይድ መሐመድ አብዲሌን የሚዘክር መድረክ በጅግጅጋ ተካሄደ

ጅግጅጋ ህዳር 10/2011 የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎችን በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በመታገል የሚታወቀው አርበኛና ገጣሚው ሰይድ መሐመድ አብዲሌን የሚዘክር መድረክ በጅግጅጋ ከተማ  ትናንት ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ እንደተገለጸው ሰይድ ቅኝ ገዥዎች በወረራነት ሲመጡ ሕዝቡን አስተባብሮ የተዋጋ አርበኛ ብሎም ሕዝቡን በግጥሞቹ ያነሳሳ ነበር፡፡ ወጣቱ ትውልድ አገሩን ከጠላት ለመከላከል ያለውን ዝግጁነት ለማዳበርና የሰይድን ጀግንነትና ግጥሞች ለማስተዋወቅ መድረኩ መዘጋጀቱን የተናገሩት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤልያስ አቢብ ናቸው፡፡ የክልሉ መንግሥት ግጥሞቹ የአገር ሀብት በመሆናቸው ለመጪው ትዉልድ በሰነድ መልክ ለማስቀመጥ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በመድረኩ ግጥሞቹን ያቀረቡት ገጣሚ አቶ አህመድ ፋራህ የአርበኛው ሰይድ ግጥሞች በአብዛኛው በጀግንነት፣ በአገር ፍቅር፣ በመስዋዕትነትና በመከባበር ላይ ያተኩሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ገራድ ኮልሚዬ ገራድ መሐመድ በበኩላቸው ሰይድ ማለት የሶማሌ ፀረ ወራሪዎች አንድነት መገለጫ በመሆኑ በጅግጅጋ ከተማ ያለው የአርበኛው ሐውልት ህያው ምስክር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በመድረኩ ሶማሌኛ ተናጋሪ ሕዝቦች ካሉባቸው ከኬንያ፣ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲና ከሶማሌላንድ የመጡ እንግዶች ተካፍለዋል፡፡ በጅግጅጋ ከተማ በሰይድ መሐመድ አብዲሌ የተሰየመ አዳራሽም ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም