በአዲስ አበባ ለገሀር አካባቢ ዘመናዊ የመንደር ግንባታ ሊከናወን መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 የአቡዳቢው ኤግል ሒልስ ሬል ስቴት ኩባንያ በአዲስ አበባ ለገሃር አካባቢ ዘመናዊ የተቀናጀ የመኖሪያ፣ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ልማት ግንባታውን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት ዛሬ ጀምሯል። ለገሀር ከፈረንሳይኛ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜዉም የባቡር ጣቢያ ማለት ነው። በአዉሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1917 የተጠናቀቀው ጣብያዉ ለከተማዋ ብሎም ለኢትዮጵያ ዋነኛው የባቡር ትራንስፖርት ማእከልም ነበር። ይህ በ360,000 እስኩዌር ሜትር መሬት ላይ የሚያርፈዉ የለገሐር የተቀናጀ የልማት ኘሮጀክት የአዲስ አበባን መሐል ከተማ ወካይ ሆኖ በዉስጡ ከ4000 በላይ መኖሪያ ቤቶች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ግዙፍ የንግድ ማእከላት፣ መጋቢና ዋና መንገዶች እና ሌሎች ዘመናዊ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ይኖሩታል። ከቦሌ አለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ በቅርብ ርቀት የሚሰራው ይህ ሁለገብ መንደር  ባለ አምስትና አራት  ኮከብ ሆቴሎች፣ አረንጓዴ መዝናኛ ስፍራዎች፣ ምቹና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች እና የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች በበቂ ሁኔታ በዉስጡ እንዳካተተም ተጠቅሷል። ኘሮጀክቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በዱባዩ ኤግል ሒልስ ትብብር የሚሰራ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች አሁን ባሉበት ቦታ መኖርያ ቤት ተገንብቶላቸዉ በዘላቂነት በሚያዉቁት ቀዬ እንዲኖሩም ይደረጋል። የኤግል ሒልስ ሊቀመንበር ሞሀመድ አልባር "ኢትዮጵያ በባህል፣ ታሪክ እና የተፈጥሮ ዉበት የበለፀገች ነች፤ ከአፍሪካ ድብቅ እንቁዎች አንዷ ናት" ብለዋል። የእኛ ፍላጎት ዉብ ከሆኑት የአገሪቱ ትሩፋቶች አንዱ የሆነውን የለገሃር አካባቢ አልምቶ አለም እንዲያውቀው እና ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ሰዎች ሁሉ ነገር በተሟላለት መንደር መኖር፣ መዝናናት እና መገብየት እንዲችሉ ማድረግም ጭምር ነው። ኤግልሒልስ በኢትዮጵያ የግል የመኖሪያ ቤቶች አልሚ ድርጅት ሲሆን ትልልቅ እሴት ያላቸው ግንባታዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ለአገሪቱ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል። ይህ በዉበቱ እና ዘመናዊነቱ የላቀ እንደሚሆን የተነገረለት መንደር በዘርፉ ከፍተኛ እውቀት አና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የሚሰራ ከመሆኑም ባሻገር የአካባቢዉን አረንጓዴነት በማገናዘብ ለመኖሪያ ምቹ በሆነ መልኩ ይገነባል። በ360,000 እስኴር ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው ፕሮጀክቱ የአነስተኛ ንግድ ስፍራዎችንም በዉስጡ የያዘ ሲሆን ዙሪያውም በመናፈሻ ፓርክ የተከለለ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ኘሮጀክቱ ለአካባቢዉ ነዋሪዎችና ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የበለጠ የማነቃቃት ሰፊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ይህ ኩባንያ ተመሳሳይ መንደሮችን በአለም ዙሪያ ለመገንባት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።ፕሮጀክቱ ሰፋፊ የሰራ እድሎችን ከመፍጠሩም ባሻገር በሀገሪቱ ያሉትን የንግድ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ ይደግፋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም