የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑና የለገጣፎ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኝውን የማዘውተሪያ ቦታ በጋራ ለመጠቀም ተስማምተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑና የለገጣፎ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኝውን የማዘውተሪያ ቦታ በጋራ ለመጠቀም ተስማምተዋል
አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የለገጣፎ ከተማ አስተዳደር በከተማ አስተዳደሩ ይዞታ የሚገኘውን የማዘውተሪያ ቦታ የአሸዋ ትራክና ጥርጊያ በጋራ አልምተው ለመጠቀም በለገጣፎ ዛሬ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉና የለገጣፎ ከተማ አስተዳደር ወይዘሮ ሐቢባ ሲራጅ የስምምነት ሰነዱን ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አትሌት ስለሺ ስህንና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ቤቱ ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያም በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል። በስምምነቱ መሰረት የአሸዋ ትራክና ጥርጊያ ሜዳ ለምቶ ለአትሌቶች ስልጠና ተግባር እንደሚውል ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኮሙኒኬሽን ደጋፊ የስራ ሂደት ክፍል የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በቅርቡም ከሁለቱም አካላት የተውጣጡበት የባለሙያዎች ኮሚቴ ተዋቅሮ የአሸዋ ትራክና ጥርጊያ በጋራ አልምተው ለመጠቀም የአፈጻጸም አቅጣጫ ተቀምጦለት የሚከናወን መሆኑም ተገልጿል።