ቀጥታ፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጠናከረ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጠናከረ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ከሀዋሳና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን የዩኒቨርሲቲዎች የማህበረሰብ አገልግሎት ትስስር ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አካሂደዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም እንደገለጹት የማህበረሰብ አገልግሎት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዋና ተግባራት አንዱ ቢሆንም በተቋማቱ አደረጃጀትና የሰው ኃይልና በጀት ምደባ አንጻር እንደ ተልዕኮ በአግባቡ አልተሰራም። በቅርቡ በአዲስ መልክ ከተቋቋመው የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር የ100 ቀናት እቅዶች መካከል ‘አንድ ቅዳሜ ለማህበረሰቤ’ በሚል ስያሜ ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በወር አንድ ቀን ቅዳሜ የማህበረሰቡን ፍላጎት በማጥናት አገልግሎት የሚሰጡበትን መርሃ ግብር ይፋ ማድረጉን አስታውቀዋል። እንደ ዶክተር ሂሩት ገለጻ መርሃ ግብሩን ለመተግበር ከዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ስምምነት የተደረገ ሲሆን በቅርቡ ይጀመራል። ሆስፒታሎች፣ የህጻናት ማሳደጊያና የአረጋውያን ድጋፍ መስጫ ማዕከላት፣የግብርናና ሌሎች ስራዎች ተማሪዎች ከሚሳተፉባቸው አገልግሎቶች መካከል መሆናቸውም ተጠቅሷል። በትምህርት ክፍሎች አስተባባሪዎች አማካኝነትም አገልግሎቶቹን የማስተባበርና ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ስራዎች እንደሚከናወኑም ነው የገለጹት። የማህበረሰብ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ብቻ ሳይሆን የተማሪዎችን ክህሎት፣ሰብዕና፣ዕውቀት፣ ህብረ ብሄራዊነትና የአገር ፍቅር የማጎልበት የጎላ ሚና እንዳለውም ዶክተር ሂሩት ገልጸዋል። በአገሪቷ 48 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከ750 ሺህ በላይ ተማሪዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህንን እምቅ ሀይል መጠቀም አስፈላጊ ነው ብለዋል። በማህበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ምርጥ ተሞክሮ ያላቸውን አገራት ልምድ በመውሰድም አገልግሎቱን የማጠናከር ስራ እንደሚሰራ ነው ሚንስትሯ የተናገሩት። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሀና እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው መመሪያ የሌለው በመሆኑ ጠንካራ የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የማህበረሰብ አገልግሎት ፖሊሲ አዘጋጅቷል ብለዋል። ይኸውም የተጠናከረ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችልና አገልግሎቱን  በዩኒቨርሲቲው ሁሉም መዋቅሮች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ነው ያሉት። ፕሮፌሰር ጣሰው እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ለመስራት ስምምነት እያደረገ ሲሆን፤ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርትና ነጻ የህግ አገልግሎቶች ላይ ለመሳተፍም አቅዷል። በተያዘው ዓመት በሶስት የመሰናዶና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የዩኒቨርሲቲው መምህራን ስልጠና እንዲሰጡ መታቀዱንም ገልጸዋል። መምህራን ቢያንስ በዓመት 20 ቀን እንዲሁም ተማሪዎች በየወሩ አንድ ቀን የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግም አክለዋል። በአሜሪካ ኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ስራ ላይ የተሰማሩት ዶክተር አሰፋ ገብረአምላክ በበኩላቸው በአውሮፓና አሜሪካ የግብርና ጤና የኤክስቴንሽን ስራዎች የሚከናወኑት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሆኑን ተናግረዋል። አሜሪካ በዚህ የ100 ዓመት ልምድ ያላት ሲሆን ይህም ለኢትዮጵያ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ልምዳቸውን ለማካፈልና አብረው ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከምርምርና ማስተማር ስራዎች በተጨማሪ የማህበረሰብ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቋማት ግን በማስተማርና በምርምር ስራዎች ነው ታጥረው ያሉት ብለዋል። የአገሪቷን ዕድገት ማፋጠን የሚቻለው የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረጉና ችግር ፈቺ አገልግሎቶች መስጠት ሲቻል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም