ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድን በዓል ሲያከብር ለአገር ሰላምና አንድነት ጸሎት በማድረግ ሊሆን ይገባል-የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት

አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድን በዓል ሲያከብር ለአገር ሰላምና አንድነት ጸሎት በማድረግ ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ። ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀረበው 1493ኛውን የነብዩ መሃመድ የልደት በዓል (መውሊድ)ን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ ነው። ነብዩ መሃመድ መረዳዳትና መፈቃቀር የእስልምና መሰረታዊ ክፍል እንደሆነ ማስተማራቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ ህዝበ ሙስሊሙ ይህን አስተምሮ ዘወትር መጠበቅ እንዳለበት አትቷል። ህዝበ ሙስሊሙ ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የመቻቻልና የመከባባር ባህልን ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባውም ምክር ቤቱ በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል። አንድነት፣ ፍቅርና መተባበር በእስልምና ትልቅ ቦታ ያለው በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብረ  ለአገር አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር ጸሎት በማድረግ መሆን እንደሚገባም በመግለጫው ተመላክቷል። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በመካከላቸው ተከስቶ የነበረውን ችግር በመፍታት ወደ አንድነት እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለአበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርቧል። ህዝበ ሙስሊሙ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ በአማኞች መካካል አንድነትን ለማምጣት በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ የበኩሉን ድርሻ አንዲወጣም ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። ኢትዮጵያ እስልምናን አስቀድመው ከተቀበሉ አገራት አንዷ ስትሆን በተለይ የነብዩ መሃመድ የልደት በዓል መውሊድ በኢትዮጵያ በተደራጀ መልኩ  እንዲከበር አሻራ የጣሉት ደግሞ  ሸህ መሃመድ አልሻፍ(ጀማንጉስ) ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም