ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሁለትዮሽ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሁለትዮሽ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል
አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 ከ11ኛው የአፍሪካ ህብረት አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙ የአፍሪካ መሪዎችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር እንዲወያዩ ምቹ ሁኔታ ፈጥራል፡፡ ትኩረቱን በህብረቱ ተቋማዊ ለውጥ ስራዎች ላይ አድርጎ ሲመክር የቆየው 11ኛው የአፍሪካ ህብረት አስቸኳይ የመሪዎች ጉበኤ ትናንት ተጠናቋል። የአህጉሪቷን መሪዎች በአንድ ጣራ ስር ያሰባሰበው ጉባኤው እኤአ ከ1993 ጀምሮ ሲጓተት የነበረው የሰላም ፈንድ በአዲስ መልክ ስራ እንዲጀምር የወሰነ ሲሆን፤ ለፈንዱም ባላደራ ቦርድ መቋቋሙን የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ይፋ አድረገዋል። ጉባኤው ህብረቱ በፋይናስ እራሱ እንዲችል በሚያደርገው የ0.2 በመቶ የገቢ ታክስ መዋጮ ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጉም ሊቀ መንበሩ ገልጸዋል። በህብረቱ የሰው ሃይል ድልድል ሁሉንም አገራትና ቀጣናዊ የልማት ኮሚቴዎችን ባማከለ መልኩ እንዲሰራና የአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት (ኔፓድ) የህብረቱ የልማት ኤጀንሲ እንዲሆን መወሰኑም ሌላው የጉባኤው ውጤታማ ቆይታ ማሳያ ነው። በዚህ ውጤታማ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የበርካታ አገሮች መሪዎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክ ውይይቶች አካሂደዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በሁለት ቀናት ውስጥ የስድስት የአፍሪካ አገሮችን ፕሬዚዳንቶችን በጽህፈት ቤታቸው ማነጋገራቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ዘግቧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅዳሜ ህዳር 7 ቀን 2011ዓ.ም ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ ከጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ እና ከጋናው ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ ጋር በአህጉራዊ ጉዳዮችና የጋራ የትብብር አቅጣጫዎች ላይ ተወያይተዋል። መሪዎቹ ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ እየተያ ያለው ለውጥ ለአህጉሪቷ ስለሚኖረው አስተዋጽኦም ምክክር አድርገዋል። ህዳር 9 ቀን 2011ዓ.ም ደግሞ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ እና የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልባሽርን እንዲሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከዚህ በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና ጄ ሞሃመድን ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተወያይተዋል። በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በነበራቸው ቆይታም ከግብጹ አቻቸው ሙስጠፋ ማድቦሊ ጋር የሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ መምከራቸውም የሚታወስ ነው።