ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ነገ በጅቡቲ ከሶማሊያ ጋር ያደርጋል

አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዞን የኦሎምፒክ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከሶማሊያ አቻው ጋር ይጫወታል። ጨዋታው በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ የሚደረግ የማጣሪያ ጨዋታ ነው። በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ ከሶማሊያ አቻው ጋር የመልስ ጨዋታውን ነገ በጅቡቲ ብሔራዊ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ያደርጋል። ጨዋታው በጅቡቲ የሚካሄደው የሶማሊያ የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ነው። ህዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ከነዓን ማርክነህ፣ እስራኤል እሸቱና አቡበከር ሳኒ በጨዋታ አማኑኤል ገብረሚካኤል በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠሩት ግቦች የሶማሊያ አቻውን 4 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል። በጨዋታው በቀይ ካርድ ከሜዳው የተሰናበተው አቡበከር ሳኒ በነገ ጨዋታ ላይ አይሰለፍም። ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ሶማሊያን ካሸነፈች በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ከማሊ ብሔራዊ ቡድን ጋር የምትጫወት ሲሆን ማሊን አሸንፋ ወደ ቀጣዩ ዙር ካለፈች በመጨረሻው ዙር ከሩዋንዳ፣ ሞሮኮና ዴሞክራቲክ ኮንጎ አንዳቸውን ታገኛለች። ይህን ዙር ካለፈች ደግሞ በታህሳስ 2012 ዓ.ም በግብፅ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ አገሮች የኦሎምፒክ ውድድር የምትሳተፍ ሲሆን በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ከወጣች ለቶኪዮ የእግር ኳስ ውድድር በቀጥታ አልፋ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሎምፒክ እግር ኳስ ውድድር ትሳተፋለች ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም