ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን 27 በመቶ ወጪን በውስጥ አቅም ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው

ደብረማርቆስ ህዳር 10/2011 የምስራቅ ጎጃም ዞን ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዞኑን ወጪ 27 በመቶ በራሱ የውስጥ አቅም ለመሸፈን የሚያስችል ገቢ እየሰበሰበ መሆኑን አስታወቀ። የጽፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት በቀለ ለኢዜአ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ከ812 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው። በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ268 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደቻለም ተናግረዋል። በሩብ ዓመቱ የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ48 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው የጠቆሙት ኃላፊዋ "ይህም ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግብር አስቦ የመክፈል ልምዱ እያደገ መምጣቱን ያሳያል" ብለዋል። ወይዘሮ ገነት እንዳሉት ገቢው የተሰበሰበው በዞኑ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሰማርተው ከሚገኙ 35 ሺህ የደረጃ "ሀ"፣ "ለ" እና "ሐ" ግብር ከፋዮች ነው። በቀሪ ወራቶች ከምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ የሚመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የታቀደውን ገቢ ለማሳካት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ከሚሰበሰበው ገቢም ለዞኑ ከሚመደበው ዓመታዊ በጀት 27 በመቶ የሚሆንውን በውስጥ ገቢ ለመሸፈን መታቀዱን አብራርተዋል። ከግብር ከፋዮች መካከል የአነደድ ወረዳ ነዋሪ አቶ ደርቤ ይስማው ግብር መክፈል አገራዊና ህዝባዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በመረዳታቸው በየዓመቱ ያለማንም ቀስቃሽ ግብራቸውን በመክፈል ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። "በቀጣይም ሥራዬን አጠናክሬ በመቀጠል ለመንግስት የሚጠበቅብኝን ግብር ሳልቀንስ ለመክፈል ወደኋላ አልልም" ብለዋል። የደጀን ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ እናቴነሽ ብርቁ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በተነሳሽነት ግብር ለመክፈል ፍላጐት እንዳልነበራቸውና ግብር ሰብሳቢዎች ሲመጡም ሱቃቸውን እየዘጉ ይጠፉ እንደነበር ጠቁመዋል። "ድርጊቱን ግብር መከፈል የራስ ልማት መሆኑን ሳልገነዘብ በመቅረቴ ስፈጽመው ነበር " ያሉት ወይዘሮ እቴነሽ ዘንድሮ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ የተጣለባቸውን ግብር ቀድመው መክፈላቸውን አስረድተዋል። በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ማከናወን እንደተቻለም ከጽህፈት ቤቱ የተገኝው መረጃ ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም