የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ህዳር 10/2011 12 ክለቦችን የሚያሳትፈው የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ይካሄዳሉ። ፕሪሚየር ሊጉ ትናንት በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች መጀመሩ ይታወቃል። በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት አዲስ አበባ ከተማ ከጥረት ኮርፖሬት ከቀኑ 11 ሰአት ኢትዮ-ኤሌትሪክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር ህዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 11 ሰአት ላይ ጨዋታውን ያደርጋሉ። ትናንት ሊጉ ሲጀምር በተካሄዱ ጨዋታዎች በሃዋሳ ሰው ሰራሽ ስታዲየም ጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች አካዳሚን ያስተናገደው ሃዋሳ ከተማ 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል። በዲላ ስታዲየም ጌዲኦ ዲላ ድሬዳዋ ከተማን በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ መከላከያን በተመሳሳይ 2 ለ 1 ማሸነፍ ችለዋል። ደደቢት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች አንደኛ ዲቪዚዮን ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። ያለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ በመሆን የበላይነት ይዞ የነበረው የደደቢት የሴቶች እግር ኳስ ክለብ ባጋጠመው የፋይናንስ ችግር ምክንያት በዘንድሮው ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ እንደማይሳተፍ ማሳወቁ ይታወሳል። የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።