ሕገ ወጥ መድኃኒትና የምግብ ምርቶችን ለመቆጣጠር እየሰራሁ ነው-ባለሥልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
ሕገ ወጥ መድኃኒትና የምግብ ምርቶችን ለመቆጣጠር እየሰራሁ ነው-ባለሥልጣኑ
ጅማ ህዳር 9/2011 በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሕገወጥ መድኃኒትና የምግብ ምርቶችን በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ። ባለሥልጣኑ በጅማ ከተማ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለመድኃኒት ቁጥጥር ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ ሥልጠናው እየተካሄደ የሚገኘው ''የድካማችን ዋጋ የህዝባችን እርካታ ነው!" በሚል መሪ ሐሳብ ነው፡፡ የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ከይረዲን አማን ሥልጠናውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ተቋሙ የሕዝቡን ጤና የሚጎዱ የመድኃኒትና ምግብ ምርቶች ዝውውር ለመግታት በተያዘው በጀት ዓመት ጠንክሮ ይሰራል። ኅብረተሰቡ በተለይ ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ የምግብ ምርቶች፣ የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ በሆኑና ፈዋሽ ባልሆኑ መድኃኒት ከሚደርስበት ጉዳት አንጻር በሚያቀርበው ቅሬታ በተቋሙ ላይ ያለው እርካታ አነስተኛ እንዳደረገው ገልጸዋል። ከሥልጠናው በኋላ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለማቃለል ተግተን እንሰራለን ብለዋል፡፡ የባለሥልጣኑ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አድናን ሻሚል ሕገ ወጥ የመድኃኒትና የምግብ ንግድን፣ጥራቱ የተጠበቀ የሕክምና መሣሪያዎች አገልግሎት አቅርቦት፣ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀለ የምግብ ምርት ገበያ ላይ እንዳይውልና በአንድ ሳምንት ውስጥ የመድኃኒት ንግድ ፈቃድ የሚሰጥበት አሰራር ለመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ሁለት ሺህ ባለሙያዎችን በሁለት ዙሮች ማሰልጠንና 10 ከመቶ ለሚሆኑት የጤና ተቋማት ላይ ቁጥጥር ማድረግ በኅዳርና በታኅሣሥ ወራት እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡ የቁጥጥር ሥራው ባለሙያዎች ወጥ በሆነ መንገድ ሪፖርት የሚያደርጉበት እንደሚሆንና ለተመሳሳይ ችግርም ተመሳሳይ ውሳኔ እንደሚሰጥበት አቶ አድናን አስታውቀዋል፡፡ ከጋምቤላ ክልል መንግሽ ወረዳ ጤና ጣቢያ የመጡት አቶ ታምሩ ረጋሳ የመጠቀሚያ ምርታቸው ያለፉባቸውን ምርቶች ገበያ ላይ እንደሚውሉ ከኅብረተሰቡ ጥቆማና በሥራቸው እንደሚያውቁ አመልክተው፣በነዚህ ደረጃቸውን ባልጠበቁና ምንጫቸው ባልታወቁ መድኃኒቶች ሳቢያ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ ከጅማ ዞን መቾ ወረዳ ጤና ጣቢያ የመጡት ወይዘሮ መሳይ ዓለሙ የሕገ ወጥ መድኃኒትና የተበላሹ የምግብ ምርቶች ዝውውር እየተስፋፋ በመምጣቱ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በሐቀኝነት መሥራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ሥልጠናው ችግሩን በዚህ ዓመት ለማቃለል የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚያግዝ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡