ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ቤተክርስቲያኗ ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ቤተክርስቲያኗ ድጋፍ አደረገች
ዲላ ህዳር 9/2011 በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የደቡብ ሲኖዶስ በጌዴኦ ዞን ለሚገኙና ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ለተመለሱ ዜጎች 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡ የቁሳቁስ ድጋፉ የተደረገው በገደብ ወረዳ ሀርሙፎ ቀበሌ ለሚገኙ ተመላሽ ለ414 አባውራና እማውራዎች ተፈናቃዮች ነው ፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ደቡብ ሲኖዶስ ፕሬዚዳንት ቄስ ወልዴ አየለ "የሚጠበቅብንን ለማድረግና የተቸገሩትን መርዳት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በመሆኑ ድጋፉን ልናደርግ ችለናል" ብለዋል ፡፡ ዲላ በሚገኘው የደቡብ ሲኖዶስ ከዚህ በፊት በፀጥታው ችግር ምክንት ተፈናቅለው ወደ ጌዴኦ ዞን ለመጡ ዜጎች 270 ሺህ ብር የሚገመት የዱቄትና ዳቦ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል። " ከዚህ በተጨማሪም የሲኖዶሱ አጋር የሆኑና በውጭ አገር የሚገኙ ክርስቲያናዊ ተራድኦ ድርጅቶችን የማስተባበር ሥራ ስንሰራ ቆይተናል " ያሉት ቄስ ወልዴ ከነዚህ ድርጅቶች በተሰበሰበው ገንዘብ ተፈናቅለው በዞኑ ለሚገኙ ዜጎች በርካታ ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል ፡፡ አሁን የተደረገው ድጋፍ ከቄያቸው ተፈናቅለው ለተመለሱ ወገኖች መሆኑን የተናገሩት ቄስ ወልዴ በእዚህም ዋጋቸው 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ብርድልብስ፣ ማጠቢያ፣ ጀሪካን፣ ማንቆርቆሪያና ሌሎች እቃዎች ለ414 ተመላሽ ተፈናቃዮች መለገሱን ገልጸዋል። ቤተክርስቲያኗ ከምታደርገው ሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር ሕብረት በመፍጠር ህዝቡን የማረጋጋትና የማስተማር ሥራዎችን ስትሰራ መቆቷንም አስረድተዋል። ከእዚህ በተጨማሪም በዲላና በቡሌ ሆራ የሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ሲኖዶሶች በመጣመር የሠላም ትምህርትና ሥልጠና ለአካባቢው ማህበረሰብ ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ቄስ ወልዴ ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የደቡብ ሲኖዶስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ተድላ አረጋ በበኩላቸው ሲኖዶሱ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ሌሎች የተራድኦ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተግባራዊ ለመሆን በሂደት ላይ የሚገኙ ድጋፎችን ጨምሮ እስካሁን ለተፈናቃዮች 7 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የበጎ ምግባር ሥራዎችን ማከናወኑንም አስረድተዋል፡፡ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ በቀጣይም ሲኖዶሱ ተመሳሳይ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ነው አቶ ተድላ የጠቆሙት፡፡ የእምነት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የዞንና ወረዳ አስተዳደሮች ለተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ በብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ምላሽና መልሶ ማቋቋም ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታዬ ጌታቸው ናቸው። እድሮችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችም ለተፈናቃዮች አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ነው የገለጹት፡፡ ተፈናቃይ ዜጎች የወደሙ ቤቶቻቸው ተሰርተው መደበኛ ሕይወታቸውን እስኪጀምሩ ድረስ በተለያዩ አካላት የሚደረጉ ሰብዓዊ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ አበበች ሉኦ በገደብ ወረዳ ሀርሙፎ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጊንዳ ከሚባል አዋሳኝ አካባቢ በወቅቱ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል፡፡ በጸጥታ ቸገሩ ቤት ንብረታቸው በመቃጠሉ በወረዳው ሌሎች ቀበሌዎች ተፈናቅለው የቆዩት ወይዘሮ አበበች በአሁኑ ወቅት አካባቢው ተረጋግቶ ወደቄያቸው ቢመለሱም ምንም ስለሌላቸው በእጅጉ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ በቤተክርስቲያኗ የተደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸውን በተወሰነ ደረጃ የሚያቃልልላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን የገለጹት ወይዘሮ አበበች፣ የተቃጠለ ቤታቸው በፍጥነት ተሰርቶላቸው ወደ ቀድሞው ሕይወታቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ፡፡