ቀጥታ፡

የአፍሪካ የሠላም ፈንድ በአዲስ መልክ ሥራውን ጀመረ

አዲስ አበባህዳር 9/2011 የአፍሪካ ኅብረት የሠላም ፈንድ ትናንት አዲሰ አበባ ውስጥ በተከናወነ ስነ-ስርዓት ሥራውን በአዲስ መልክ በይፋ ጀምሯል። የፈንዱን ሥራ መጀመር ይፋ ያደረጉት የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀ-መንበር ፖል ካጋሜና የኅብረቱ ኮሚሽነር  ሙሳ ፋቂ ማኅማት ናቸው። የአፍሪካ የሠላም ፈንድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ1993 ጀምሮ ቢመሰረትም ወደ ሥራ የገባው ግን ከጥቂት ዓመታት በፊት መሆኑም ተጠቁሟል። ፈንዱን ለማጠናከርም አገራት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ እንዲያዋጡ ለማስቻል ከትላንት በስቲያ የሠላም ፈንዱን የሚመራ  የባለአደራ ቦርድ ተቋቁሞለታል። ባለአደራ ቦርዱም ከአህጉሪቱ አምስት  ከመንግሥታቱ ድርጅትና ከአውሮፓ ኅብረት ደግሞ ሁለት ግለሰቦችን በመያዝ ሥራውን በይፋ ጀምሯል። የሠላም ፈንዱ በሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ላይ የሚሰሩ የአህጉሪቱ ተቋማት አሰራር ማጠናከርና የሰው ኃይል ማጎልበት ላይም ትኩረት እንደሚያደርግ ተገልጿል። ፈንዱ ግጭትን ለመከላከል፣ የማስታረቅና የድርድር ሥራ ለመሥራት እንዲሁም ግጭት ሲፈጸም የሠላም አስከባሪ ሥራ ይሰራልም ተብሏል። ከዛም በዘለለ የሰላም ማጎልበት ሥራና እንዲሰራና ኅብረቱ አልያም ደግሞ አፍሪካውያኖች ጉዳያቸውን የራሳቸው ማድረግ የሚችሉበት መሆኑን አስረድተዋል። የሠላም ፈንዱ በይፋ መከፈቱ ኅብረቱ የጀመረውን አጠቃላይ የተኃድሶ እንቅስቃሴ እንደሚደግፍና የለውጡ ሂደት አካል መሆኑም ነው የተጠቀሰው። ኅብረቱ ከአምስቱ የኅብረቱ ቀጠና ለሠላም ፈንዱ በተናጠል በዓመት 80 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 325 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ አቅዷል። ይህንንም አሃዝ ከሁለት ዓመታት በኋላ 400 ሚሊዮን ለማድረስ ያቀደው ኅብረቱ መዋጮው የሚሰበሰበው አገራት ከውጭ ከሚያስገቡት እቃ ከሚያገኙት የ0 ነጥብ 2 ገቢ በመሰብሰብ መሆኑ ተጠቅሷል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም