ፉክክር አልባ ጨዋታዎች እና ጸብ ቀስቃሽ አስተሳሰቦች የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቱን አባብሰውታል - ኢዜአ አማርኛ
ፉክክር አልባ ጨዋታዎች እና ጸብ ቀስቃሽ አስተሳሰቦች የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቱን አባብሰውታል
ህዳር 8/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፉክክር አልባ መሆን፣ የእግር ኳስ ህግጋት አለመከበር እንዲሁም ጸብ ቀስቃሽ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችን ይዞ ወደ ስታዲየም መግባት የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሩን አባብሶታል ይላሉ ያናገርናቸው ምሁራንና ተመልካቾች። ከ1990ዎቹ ጀምሮ እስከ ቅርብ አመታት የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮችን ሲመለከት እንደነበር የገልፀው አቶ ለማ ጅሚቱ የውድድሮች መዳከምና ብሄርተኝነት ላይ የተመሰረተ ብጥብጥ ከስታዲየም አርቆኛል ነው ያሉት። ቀደም ሲል የነበሩ ውድድሮች ስሜት የሚይዙ እና በብቃት ላይ የተመሰረተ ፉክክር የሚደረግባቸው፤ ድጋፉም ስፖርታዊ ጨዋነትን የተላበሰ በመሆኑ ለአላስፈላጊ አምባጓሮዎች ጊዜ አይኖርም ነበር በማለት ይገልጻሉ። እግር ኳስ” መዝናኛ እንጂ የብጥብጥ እና የጥላቻ ማንጸባረቂያ መድረክ” መሆን የለበትም ያሉት አቶ ለማ፤ አንዳንድ ክለቦች በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት ከመጫወት ይልቅ በገለልተኛ ሜዳ እንዲጋጠሙ መደረጉ መፍትሔ የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል። የዳኝነት ስህተት፣ የተጫዋቾች ስነምግብር ችግር እንዲሁም ማሸነፍን ብቻ አስበው ወደ ስታዲየም የሚገቡ ደጋፊዎች ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መነሻ እንደሆኑ መታዘቡን የገለጸው ደግሞ ወጣት አቡበከር አደም ነው። በተወሰኑ ደጋፊዎች መካከል የዘረኝነት ስድቦች መንጸባረቃቸው ለሰላማዊ ውድድር ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውንም ወጣት አቡበከር ይገልጻል። የፕሪሚየር ሊጉ ቋሚ ተመልካች የሆኑት አቶ ደጀኔ ሀይሉ በበኩላቸው ከጥቂት አመታት ወዲህ ስታዲየሞች ውስጥ በሚፈጠረው ፀብ ሰዎች ለከፋ ጉዳት ሲዳረጉ እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ሲደርስ ተመልክቻለሁ ነው ያሉት፡፡ ከአመታት በፊት ልጆቻቸውን ለማዝናናት ስታዲየም ይዘው የሚገቡ ወላጆች ግፊያና ብጥብጡን በመፍራት ከሜዳ እየራቁ እንደሆነ ነው የገለፁት። በውድድር ወቅት የሚስተዋሉ አደንዛዥ እጾችን ተጠቅሞ ስታዲየም መግባት ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጠ፤ ለእግር ኳሱ እድገትም እንቅፋት በመሆኑ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባልም ይላሉ። ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማስፋፋት የክለብ ደጋፊዎች ለተጋጣሚያቸው ክብር መስጠት፣ ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን መመዘግብ፣ ህጋዊ ማድረግና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት ለችግሩ አንዱ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል። በፕሪሚየር ሊግ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መታየት መጀመሩን የጠቀሱት የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ስዩም ተሾመ የሁሉም ክለቦች አመራሮች ስፖርታዊ ጨዋነት ምን እንደሆነ ደጋፊዎቻቸውን አስቀድመው ማስተማር አለባቸው ይላሉ። እንደ መከላከያ ክለብ “በቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ እያለን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጋር በመተባበር ተጫዋቾች የዳኝነት ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርገናል” ነው ያሉት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ዙሪያ ጥናት ያካሄዱት ዶ/ር አለምመብራት ክፍሉ በውድድር ስፍራ ጥሩ ስነምግባርን ያልተላበሱ ማናቸውም አካላዊም ሆነ አዕምሯዊ አካሄዶች የስፖርታዊ ጨዋነት ጎጂ ምልክቶች መሆናቸውን ነው የጠቀሱት፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ የሚታየው ሁከት እየተስፋፋ መምጣቱ ስፖርት ለሰላም፣ የአንድነት እና ለፍቅር የሚለው የኦሎምፒክ መርህ እንዲጣስ እድርጓልም ይላሉ፡፡ ሜዳ ላይ ቀልብ የሚስብ ፉክክር መጥፋት፣ በዳኞች ላይ የሚታይ የአቅም ማነስ፣ ደጋፊ ድልን ብቻ መፈለጉ፣ ብሄር ተኮር የጥላቻ ንግግሮች እና አብዛኛው ተመልካች ወጣት መሆኑ በተጨባጭ በጥናታቸው ውስጥ የዳሰሷቸው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች መሆናቸውን ዶ/ር አለምመብራት ይጠቁማሉ፡፡ “በወጣቶች ላይ ስሜታዊነት ይታያል የሚሉት” ዶ/ር አለምመብራት አልኮሆል ወስደው ስታዲየም የሚገቡም እንዳሉ በጥናታቸው መዳሰሳቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ፌዴሬሽኑ ተጫዋቾች የጨዋታ ህግ እና ደንብ እንዲያከብሩ፣ ዳኞችም ጥራት ያለው ዳኝነት እንዲሰጡና ተመልካቹም የእግር ኳስ እውቀቱ እንዲዳብር ስልጠናዎች ከፌዴራል እስከ ክልል ሊሰጥ እንደሚገባም ዶ/ር አለምመብራት መክረዋል። ሌላው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር ሳህሌ ሚካኤል ስፖርታዊ ጨዋነት አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሁለቱ ተጋጣሚ ቡድን ደጋፊዎች ብጥብጥ ላለማስተናገድ እኩል ሃላፊነት መውሰድ አለባቸው ነው ያሉት። ሁከት እና ብጥብጥን ለመከላከል ሀላፊነቱ የፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ክለቦች፤ የክለብ ሀላፊዎችና፣ የደጋፊ ማህበራት ደጋፊዎቻቸውን የመቆጣጠር ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም ነው ዶ/ር ሳህሌ የሚገልፁት፡፡ “ምዕራባውያን የስፖርታዊ ውድድሮችን ህግ እና ደንቦችን ማክበር እንደ ትልቅ እሴት ነው የሚቆጥሩት፤ እኛም ሀገር የሞራል ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል” ሲሉ ነው የጠቆሙት፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ባለፉት ጥቂት አመታት እግር ኳሱን እየፈተነ የሚገኘውን ረብሻ እና ሁከት ለመከላከል ክለቦች ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ ከነጥብ ቅነሳ ጀምሮ ከውድድር እስከማገድ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ነው የገለፀው። የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም እንዳሉት በዚህ ዓመት በስፖርታዊ ጨዋነት ውድድራቸውን የሚያጠናቅቁ ክለቦችን ለማበረታታት ሽልማት ይበረከትላቸዋል። “እንደ ተጫዋች የስፖርታዊ ጨዋነትን ማክበር አለብን” ያለው በ2010 ዓ.ም የውድድር አመቱ ልዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚው የመከላከያ ተጫዋች ፍጹም ገ/ማርያም ከዚህ በፊት የነበረው የደጋፊዎች ግጭት በዚህ ዓመት ሊቆም ይገባል ብሏል። ፍጹም መከላከያ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በዳኛው እና ተጫዋቾች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ባደረገው ጥረት ነው የዓመቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚ የሆነው። ዘንድሮ ለ21ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2011 ዓ.ም መርሀ ግብር ሲዳማ ቡና ከፋሲል ከነማ ባደረጉት ጨዋታ መጀመሩ ይታወሳል፡፡