ቀጥታ፡

በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ መሰራት አለበት

አዲስ አበባ ህዳር 8/2011 በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ መሰራት እንዳለበት ተነገረ። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል። የትግራይ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሃፍቶም ገብረሚካኤል ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ላይ የታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈቶችን አንስተዋል። አሰልጣኞች ቅሬታ ማቅረብ የሚገባቸው ከጨዋታ በኋላ ለኮሚሽነሩ ሆኖ ሳለ ህጉ በማይፈቅደው መልኩ ጨዋታዎች ላይ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ወደ ዳኞች በመሄድ ተቃውሞ ማቅረብና የዳኞችን ጠረጴዛ በመደብደብ ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር መፈጸሙን ጠቅሰዋል። በባለፈው ዓመት ፕሪሚየር ሊግ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ላይ የመከላከያ ተጫዋቾች ዳኛ በመደብደብ የፈጸሙት ተግባር ጎልቶ የታየ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እንደሆነም በማሳየነት ጠቅሰዋል። አሰልጣኞችም ሆነ ተጫዋቾች ስፖርቱ ያስቀመጣቸውን የስነ ምግባር መርሆዎችና ህጎች ማክበር እንዳለባቸውና የስፖርታዊ ጨዋነት ጥፋት የሚፈጽሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አመልክተዋል። በሌላ በኩል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለክልሎች የሚያደርገው የቁሳቁስ ድጋፍ ዝቅተኛ በመሆን በዚህ ላይ በትኩረት መስራት አለበት ብለዋል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ዳኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንስትራክተር ደስታ በርሄ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ከስፖርተኞች ስነ ምግባር አንጻር በታየው ችግር ምክንያት የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዳኞች ስቃይ ያዩበት ጊዜ እንደነበር ተናግረዋል። በዳኞች በኩል ባሉ የአቅም ክፍተቶች ምክንያት የውሳኔ መዛባቶች እንደነበሩና ውሳኔዎች ላይ ህግና ስርአት በማክበር ቅሬታ ማቅረብ ሲገባ አግባብ ባልሆነ መልኩ ዳኞች ላይ ሲቀርብ የነበረው ተቃውሞ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረባቸው ጠቅሰዋል። በክልሎች ዳኞች ሲያጫውቱ ጫና ሲፈጠርባቸው እንደነበር አውስተዋል። ችግሩ እንዳይደገም ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበትና የዳኞች ክፍያም ዝቅተኛ በመሆኑ ሊያድግ እንደሚገባው ገልጸዋል። የደቡብ ክልል እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ማቲዎስ ጉርማሞ የእጅ ኳስ ስፖርቱ ጥሩ መነቃቃት ላይ እንዳለና ስፖርቱ ይበልጥ እንዲያድግ እምቅ አቅም ባላቸው ክልሎች ላይ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋ። ክልላቸው በስፖርቱ ላይ ቢሰራበት ውጤታማ ነገር ማምጣትና ብቁ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት እንደሚቻል ገልጸው በሌሎች ክልሎች ያሉ ፕሮጀክቶችን በማጎልበት ስፖርቱን ለማሳደግ መሰራት እንደሚገባ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ የታዩ ግድፈቶች ላይ በመመሪያውና ደንቡ መሰረት አስፈላጊው እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል። ዳኛ የደበደቡ የመከላከያ ተጫዋቾች ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት እንደተቀጡ አውስተው ክለቡ በተቀጡት ተጫዋቾች ምክንያት የመፍረስ አደጋ እንዳጋጠመው ገልጾ በጠየቀው መሰረት ቅጣቱ ወደ ገንዘብ እንዲቀየርለት መደረጉን አስታውሰዋል። መካለከያም የስነ ምግባር ግድፈት በፈጸሙት ተጫዋቾች ላይ ከክለቡ እስከ ማባረር ደረጃ የደረሰ እርምጃ አንደወሰደ ጠቅሰዋል። የሚስተዋሉ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶችን ለማስወገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንና ፌዴሬሽኑም በዚህ የውድድር ዓመት ለጉዳዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በዳኞች በኩል የተነሳውን የአበል ጥያቄ ለመፍታት የፋይናንስ ደንቡን የማሻሻል ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። በጠቅላላ ጉባኤው የ2011 ዓ.ም መሪ እቅድና አዲስ የተዘጋጀው የክለብ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች የዝውውር አፈጻጻም መመሪያ ውይይት ተደርጎባቸው ጸድቀዋል። የሴቶች ፕሪሚየር ሊግን በዚህ ዓመት መጀመር፣ ክለቦች በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች በስፋት ተካፋይ እንዲሆኑ ማድረግና ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በክልሎች ቅስቃሳና ውድድሮችን ማካሄድ የበጀት ዓመቱ የትኩረት አቅጫዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም