ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በምስራቅ አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ለውጥ እያመጡ ነው - ቢዝነስ ሪፖርት - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በምስራቅ አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ለውጥ እያመጡ ነው - ቢዝነስ ሪፖርት
አዲስ አበባ ህዳር 8/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአገራቸው አልፈው በምስራቅ አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ አስደናቂ ለውጥ እያመጡ ነው ሲል ቢዝነስ ሪፖርት በዘገባው አመለከተ። ዘገባው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመዘገበውን ለውጥ በ1980 እና 1990ዎቹ ሚካኤል ጎርባቾቭ በሶቪየት ዩኒየን ካስመዘገቡት ፈጣኑ የፔሬስትሮይካ ማሻሻያ ለውጥ ጋር አነጻጽሮታል። የበርካታ ቋንቋዎች ተናጋሪው የ42 ዓመት ጎልማሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን በመጡ በወራት ውስጥ ከኤርትራ ጋር ለዓመታት የዘለቀውን የጠብ ግንብ ከማፍረስ ጀምሮ በርካታ ለውጦችን ማስመዝገባቸውን ጠቅሷል። "በዚህ ሳምንትም የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በርካታ የሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደፈፀሙ የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ በማድረግ የላቀ ውጤት አሳይተዋል" ብሏል ዘገባው። በመንግስት ስም ይፈጸም የነበረውን ጭካኔ የተሞላበት የማሰቃየት ድርጊት 'መንግስታዊ ሽብርተኝነት' ሲሉ መኮነናቸውንም ጠቅሷል። በውጭ ፖሊሲ ላይ የተከተሉት አማራጭ የተሻለ የውጭ ግንኙነት መፍጠር ያስቻለ ሰለመሆኑም ቢዝነስ ሪፖርት በድረ ገጹ አስነብቧል። ከኤርትራ ጋር ለዓመታት የዘለቀውን የሻከረ ግንኙነት ወደ ወዳጅነት መቀየር ያስቻሉ መሆናቸውን በመግለጽም አድናቆቱን ቸሯቸዋል። የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መቀየር ኤርትራ ከጅቡቲ የነበራትን ለ10 ዓመታት የቆየ አለመግባባት ለመፍታትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥሎባት የነበረውን ማዕቀብ ለማስነሳት መሰረት መሆኑንም ነው ያመለከተው። የኤርትራና የኢትዮጵያ ወዳጅነት መጠናከር ለቀጣናው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መሻሻል አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያመለከተው ዘገባው የዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት አሜሪካ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ የመን፣ ኳታር፣ ቱርክና ጂቡቲ ላይም አዎንታዊ ተጽእኖ ያሳድራል በማለት ዘግቧል።