ቀጥታ፡

የጥጥ ልማት ስራው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ማግኘት የወቅቱ ፈተና ሆኗል - ባለሀብቶች

አዲስ አበባ  ህዳር 8/2011 የጥጥ ልማት ስራው የሚፈልገው የሰው ኃይል እጥረት የወቅቱ አሳሳቢ ችግር መሆኑን በጥጥ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተናገሩ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት በጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣ አፋርና በደቡብ ኦሞ በጥጥ ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች እንደተናገሩት በዘርፉ ላይ በርካታ ፈተናዎች የተጋረጡ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሰው ኃይል እጥረት አሳሳቢው ችግር ነው። የጥጥ ምርት በተለይም በለቀማና አረም መንቀል ስራዎች ላይ በርካታ የሰው ኃይል የሚጠይቅ መሆኑን ነው የሚናገሩት። በጋምቤላ ክልል በጥጥ ልማት የተሰማሩት አቶ አብርሃም ይደግ በክልሉ በፀጥታ ችግር ሳቢያ የሰው ኃይል ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸው "በእኛ አቅም መፍትሄ ልናመጣ አንችልም፤ መንግስት እንዲያግዘን እንፈልጋለን" ሲሉ ተናግረዋል። ከቤንሻንጉል ክልል  በጥጥ ልማት የተሰማሩት አቶ ወርቅነህ ህሩይ  በበኩላቸው ለስራቸው ወደ 1 ሺህ ሰራተኛ እንደሚያስፈልግ ተናግረው ችግሩ ቶሎ መፈታት እንደሚገባውና ወቅታዊ ምላሽ እንደሚያስፈልገው አስተውቀዋል። በአፋርና በደቡብ ኦሞ ክልል የተሰማሩት ሼክ የሱፍ ኡመር ጥጥ ለቃሚ ሰራተኛ ችግር ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ መምጣቱ ይህም ለስራው እንቅፋት እየፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የጥጥ እርሻ ለአደጋ ተጋላጭ  መሆኑንና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ ተባይ፣ የእሳት አደጋና ሌሎች ስጋቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ሼክ የሱፍ በሚያመርቱባቸው አካባቢዎች ያሉትን ችግሮች ብቻ ሳይሆን እንደ የኢትዮጵያ የጥጥ አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንትነታቸውም ከአባላት የሚነሱ በርካታ ችግሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ቀልጣፋ የጉምሩክና የብድር አገልግሎት እጦት፣ የጥጥ ምርጥ ዘር አቅርቦትና የተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎች እጥረት ችግሮች መኖራቸውንም አንስተዋል። የጥጥ መዳመጫ መሳሪያዎች እጥረት፣ብልሽትና የመብራት መቆራረጥም ሌላው የጥጥ ልማት ላይ እያጋጠመ ያለ ችግር መሆኑን ገልጸዋል። በዘርፉ ከ20 አመታት በላይ ተሰማርተው የቆዩ ባለሀብቶች ባሉት ችግሮች ሳቢያ ተስፋ በመቁረጥ ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣቱንና አሁን ስራ ላይ ያሉ ባለሀብቶችም ችግሮቹ ካልተፈቱ ከዘርፉ መውጣታቸው የማይቀር መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ሼክ የሱፍ ገለፃ ችግሮቹ በግለሰቦች ደረጃ የማይፈቱ በመሆናቸው በመንግስት በኩል ፈጣን ምላሽ ካልተሰጠው የጥጥ ልማት ቀጣይነትም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው። በጋምቤላ ክልል አቶ አዳነ ስዩም እና አቶ የማነ ሰይፉ በዘርፉ በርካታ ችግሮች መጋረጣቸውንና ችግሮቹ እንዲፈቱ ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም መፍትሄ አለመገኘቱን ነው የገለጹት። በአገሪቷ ለጥጥ ምርት ተስማሚ መሬትና አየር መኖሩንና የጥጥ ልማት ስራ ደግሞ ሰፊ የስራ እድል የሚፍጥርና የውጭ ምንዛሬ ማዳን የሚቻል መሆኑ እየታወቀ ተገቢው ድጋፍ እየተደረገ እንዳልሆነም ተገልጿል። በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጥጥ ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ በሰጡት ምላሽ በጥጥ ልማት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በተለያየ ተቋማትና በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሚፈቱትን ለይተን እየሰራን ነው ይላሉ። በአሁኑ ወቅት በጋምቤላና በቤንሻንጉል ክልሎች የጥጥ ምርት መሰብሰቢያ ወቅት እየደረሰ በመሆኑ የሰው ኃይል ግን ማሟላት ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ከክልሎቹ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር እየተወያየን ነው ብለዋል። የተሻለ ምርታማነትና ጥራት ያላቸውንና ተባይን መከላከል የሚችሉ ዘሮችን ለአምራቾች ተደራሽ ለማድረግም ከምርምር ተቋማትና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል አቶ መሰለ። የጥጥ መዳመጫ መሳሪያዎች አቅርቦት ለማሻሻልም አዲስ ኢንቨስተሮችን ወደ ዘርፉ እንዲሰማሩ ማበረታቻ ድጋፍ እንዲኖር እየተሰራ በመሆኑ በቅርቡ የሚፈታ ችግር ነው ያሉት። የብድር አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሮችን ለመፍታትም ከልማት ባንክና ከብሄራዊ ባንክ ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሚፈቱትን ችግሮች ለአዲሱ አመራሮች አቅርበን ጥብቅ ክትትል እያደረግን ነው  ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም