ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ለአርሶአደሩ አማራጭ የኃይል ምንጭ እየቀረበ ነው

አምቦ ህዳር 8/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን የደን ጥፋትን ለመከላከል ለአርሶ አደሩ  አማራጭ የኃይል ምንጭ እየቀረበለት  መሆኑን የዞኑ ኢነርጂና ማዕድን ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ በጽህፈት ቤቱ የባዮ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አዱኛ ወዳጆ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የደን መመንጠር ለሀገሪቱ  አሳሳቢ በመሆኑ አማራጭ የኃይል ምንጭ መጠቀም ግድ የሚልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ባለፉት  አራት ወራት  6 ሺህ 515 ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ፣ 1ሺህ 516 በፀሐይ ኃይል የሚሰራ አማራጭ ኃይልና 12 ባዩጋዝ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አመልክተዋል፡፡ በዚህም 8 ሺህ 043 አባወራ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አርሶ አደሮችም በአካባቢያቸው የሚገኘውን ደን ለማገዶነት ከመጠቀም ይልቅ ታዳሽ ኃይልን  እንዲጠቀሙ ለማድረግ ባለፉት አራት ወራት  ለ11 ሺህ አባወራ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን አቶ አዱኛ  አስረድተዋል፡፡ በዞኑ በተያዘው የበጀት ዓመት 54 ሺህ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ፣ 4 ሺህ ሶላርና 80 አባወራዎችን  ተጠቃሚ የሚያደርግ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን ለማሰራጨት ታቅዶ ተግባራዊ እየደረገ ነው።በአምቦ ወረዳ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን መጠቀም የጀመሩት የጎሱ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጋዲሴ አደሬ በሰጡት አስተያየት "የደን መመናመን ተመልሶ የሚጎዳው እኛው አርሶአደሮች በመሆኑ አማራጭ የኃይል ምንጭን በመጠቀም አካባቢያችንን ለመታደግ ዝግጁ ነን "ብለዋል ። ሌሎች አርሶ አደሮችም ባዮጋዝ  በመጠቀም የአካባቢያቸውን ደን ከመመንጠር መታቀብ እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡ ዘንድሮ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ አማራጭ ኃይል 0መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ለኩራዝና ለባትሪ ከሚያወጡት ወጪ መገላገላቸውን የተናገሩት ደግሞ የአደአ በርጋ ወረዳ ነዋሪው አቶ አሰፋ ገልገሉ ናቸው፡፡ በተለይ ከዚህ ቀደም በኩራዝ ጭስ ይደርስባቸው ከነበረ የአተነፋፈስ ችግርና የአይን ህመም መላቀቃቸውን ተናግረዋል ። በዞኑ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ በብዛትና በጥራት አምርቶ ለማቅረብ  በ30 ማህበራት የተደራጁ 287 ወጣቶች ስልጠና ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን  ከዞኑ ኢነርጂና ማዕድን ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም