ቀጥታ፡

የወንጀል ተጠርጣሪዎችን የፍርድ ሂደት ለኀብረተሰቡ ማሳወቅ ይገባል - ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ ህዳር 8/2011 መንግስት የሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጣሪዎችን የፍርድ ሂደት ለኀብረተሰቡ በግልጽ ሊያሳውቅ ይገባል ሲሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመለከቱ። ለዓመታት ኀብረተሰቡን ሲያማርሩ የቆዩ የሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የተሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት መልካም ጅምሮች ናቸውም ብለዋል። በሙስና የተመዘበረው ሀብት ከህዝቡ ኪስ የወጣና ለትውልድ በሚተላለፍ ብድር የተገኝ በመሆኑ አላግባብ ጥቅም ላይ መዋሉ ኀብረተሰቡን ያስቆጣ ተግባር እንደሆነም ገልጸዋል። የቀድሞ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ አባል አቶ ሙሼ ሰሙ እንዳሉት ቀደም ሲል በነበሩት መሪዎች የሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ለህግ የማቅረብ ሥራ ያልተለመደ ነው። በአሁኑ ወቅት የፍርድ ሂደቱ የፍትህ ስርዓቱን ተከትሎ የሚካሄድ መሆኑና ተጠርጣሪዎችም በአግባቡ እንደሚዳኙ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ መንግስት ተዓማኒነትን እንደሚያገኝ ገልጸዋል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው በአገሪቱ ባለፉት 27 ዓመታት 'ተጠያቂነት ያለበት ስርዓት ማየት በጣም አዳጋች ነበር' ብለዋል። አሁን በሙስናና በዘረፋ ወንጀል የተሰማሩ ግለሰቦችን ወደ ህግ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ሕዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ አመኔታ እንዲኖረው ከማድረጉም ባሻገር እንደ ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበከት በር እንደሚከፍት ገልጸዋል። በፍትህ አካላት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ተከትሎ በመገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ ዘገባዎች ብሔር ተኮር እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል። ህግና ስርዓትን ተከትሎ በወንጀል ተግባራት የተሳተፉ ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ የማድረጉ እንቅስቃሴ በአገሪቱ የመጀመሪያ ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ አመራር አቶ ሌንጮ ለታ ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም