በሲኤምሲ ሚካኤል አካባቢ የድልድይ ግንባታ በመቋረጡ ነዋሪዎች ለችግር ተዳርገናል አሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሲኤምሲ ሚካኤል አካባቢ የድልድይ ግንባታ በመቋረጡ ነዋሪዎች ለችግር ተዳርገናል አሉ
አዲሰ አበባ ህዳር 8/2011 በሲ.ኤም.ሲ ሚካኤል አካባቢ በመገንባት ላይ የነበረው ድልድይ ስራ በመቋረጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ችግር እንደተፈጠረባቸው ገለጹ። በ2007 በጀት ዓመት 140 ሚሊዮን ብር ተመድቦለት ግንባታው የተጀመረው ይሕው ድልድይ በ2010 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ ተብለው ከተያዙት ፕሮጀክቶች አንዱ ነበር። ሆኖም ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ የአካባቢው ነዋሪዎች "በእለት ተለት ኑሮአችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር እየፈጠረብን ነው" ይላሉ። ከነዋሪዎች መካከል አቶ ንጉሴ ተፈሪ እንደተቆሙት በርካታ ህዝብ የሚመላለስበት ይህው ድልድይ ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ቢያስቆትርም ሊጠናቀቅ አልቻለም፡፡ በመሆኑም በመንገዱ ቶሎ አለመጠናቀቅ ሳቢያ በጊዜያቸውና በማህበራዊ ግንኙነታቸው ላ ተፅእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡ ሌላው ነዋሪ አቶ ሰለሞን በየነ በበኩላቸው መንገዱን ለመሻገር ረጅም ርቀት ለመጉዋዝና ለመኪና አደጋ ስጋት መዳረጋቸውን ተናግረው የሚመለከተው አካል አፋታን ምላሽ እንዲሰታቸው ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማሕበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደመረው ጌታቸው በበኩላቸው በድልድዩ ግንባታ አለመጠናቀቅ የማሕበሩን ህንጻ የሚፈልጉ ተጠቃሚዎችና ባለሙያዎች ለከፍተኛ ወጪና እንግልት እንደተዳረጉም ነው ያመለከቱት። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሰልጣን በበኩሉ ግንባታው የተቋረጠው በአካባቢው የባቡር ማለፊያ መንገድ በመኖሩና የዲዛይን ለውጥ ስላስፈለገው ነው ብሏል። በባለሰልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደገብርኤል ለኢዜአ እንደገለጹት ፣ግንባታው ሰፊ በመሆኑ የተለያዩ የወሰን ማስከበር ስራዎችም ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን በተያዘው የበጀት አመት የተሻለ የዲዛይን ሃሳብ ተይዞ የሚጠናቀቅ ይሆናል። የዲዛይን ሁኔታዎቹን ቀድሞ ለማወቅና ለመስራት ለምን አልታሰበበትም ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ በተጨባጭ ያሉት የዲዛይን እይታዎች መሬት ላይ ወርደው ሲሰራባቸው የሚያጋጥሙ ችግሮች ይኖራሉ ብለዋል። በበጀት አመቱ በይፋ ውል ተይዘው ወደ ስራ የተገባባቸውን 4 ፕሮጀክቶች እና የተቋረጠውን የሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ድልድይን ጨምሮ 123 የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን አቶ ጥኡማይ ገልጸዋል።