የአፍሪካ ኅብረት 11ኛው ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ኅብረት 11ኛው ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ተጀመረ
አዲስ አበባ ህዳር 8/2011 ዛሬና ነገ የሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ልዩ የመሪዎች ስብሰባ፤ ባለፈው ዓመት በተጀመረው የኅብረቱ የተኃድሶ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሏል። በተለይም የኮሚሽኑን መዋቅርና ለበርካታ ዓመታት ግልጋሎት የሰጠውን የአመራር ሥርዓትና ሁሉን አቀፍ የኮሚሽኑ አሰራር ሥርዓት ላይም ይዳሰሳል ተብሏል። የፋይናንስ ወይንም የበጀት አሰባሰብ እንዲሁም ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት (ኔፓድ) የአፍሪካ ኅብረት የልማት ኤጀንሲ ሆኖ መቋቋሙን በተመለከተም ይመክራል። የሰው ኃይል ክፍፍል በአፍሪካ ኅብረት፣ በአህጉራዊ ድርጅቶች፣ በቀጠናዊ የልማት ማኅበረሰቦችና በአባል አገራት በምን መልኩ መደልደል እንዳለበትም ይወያያሉ። ከዚህም በተጨማሪ የአፍሪካ ኅብረት የእርስ በእርስ የመገማገሚያ መድረክና የሠላምና የደኅንነት ምክር ቤት በምን መልኩ መጠናከር እንዳለበት የሚለውም ትኩረት ይሰጠዋል ተብሏል። የአፍሪካ አገራት የእርስ በእርስ ግንኙነትና የአህጉሪቱ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሊያሳልጥ የሚችል አህጉራዊ ፓስፖርት አስፈላጊነት ላይም ምክክር ያደርጋል። የፓን አፍሪካ ፓርላማ፣ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ፍርድ ቤትና ኮሚሽኑንም ለመቀየር በወጣው ረቂቅ ላይም የኃሳብ ልውውጥ እንደሚደረግ ተገልጿል። በአፍሪካ ኅብረትና ከሥሩ ባሉት ተቋማት የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ ማጎልበትም ትኩረት ይደረግበታል ተብሏል። የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ከውጭ ከሚያስገቡት እቃዎች ላይ የ0 ነጥብ 2 በመቶ የቀረጥ ገቢያቸውን ለኅብረቱ አንዲያስገቡ የሚለውን ስምምነት አፈጻጸም ላይም ውይይት ይደረግበታል። በተለይም አገራት ለሥምምነቱ ያላቸውን ቁርጠኝነት ከፍ እንዲያደርጉ የሚሉት ነጥቦች ይነሳሉ ተብሏል። በተጓዳኝም ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ሥራ አስፈጻሚዎች የመከሩባቸው ጉዳዮች ላይ ከተወያዩ በኋላ የውሳኔ ኃሳብ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።