የባህል ማዕከሉ የታለመለትን ዓላማ መምታት በሚያስችለው መልኩ እየተደራጀ ነው

62
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማዕከል የታለመለትን ዓላማ ማሳካት በሚያስችለው መልኩ እየተደራጀ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። ማዕከሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል እሴቶችና መገለጫዎች በልጽገው ለአገሪቱ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የሚያስገኙበትን ሁኔታ የመፍጠር ዓላማን ይዞ ነበር የተቋቋመው። ይሁንና ማዕከሉ የታለመለትን ዓላማ ስቶ ከስብሰባ ያልዘለሉ መርሀ-ግብሮችን ብቻ ሲያከናውን ነው ዓመታትን ያስቆጠረው። የባህል ማዕከሉ የአገሪቱ ህዝቦችን ባህላዊ እሴቶች በማበልፀግና በማስተዋወቅ ረገድ  አጥጋቢ ተግባር እያከናወነ እንዳልሆነ በሚኒስቴሩ የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛሃኝ አባተ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ለዚህም ምክንያቱ የሰው ኃይል ውስንነት፣ የፋይናንስ እጥረትና የአመራር ብቃት ማነስ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በመሆኑም ተቋሙ የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት በሚያስችለው መንገድ ዳግም ማደራጀት ማስፈለጉን አመልክተዋል። ማዕከሉ አገሪቷ ከጥንት ጀምሮ አሁን እስከደረሰችበት ያለውን ሂደት ሊያሳይ የሚችል ቁመና እንዲኖረው ተደርጎ መደራጀት አለበት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ። ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ማዕከሉን ስራ እንዲሰራ መንግስት በወሰነው መሰረት ማዕከሉን በአዲስ መልክ ለማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። የባህል እሴቶችና መገለጫዎችን በማበልፀግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከልን በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት የባህል ማዕከላት አንዱ ያማድረግ ራዕይም ተይዟል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም