ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ሰላም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

62
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 ለምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላም መስፈንና ኢኮኖሚውን ለማጎልበት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ሰላም ድጋፍ እንዲያደርግ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ ጥሪ አቀረበ። የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ዶክተር ሪክ ማቻር እና ሳልቫ ኪር ማርዲያት እ.አ.አ መስከረም 12 ቀን 2018 በአዲስ አበባ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል። የኢጋድ 66ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ሁለቱ ተቀናቃኝ መሪዎች በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት አፈጻጸም፣ በሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳይና በኢጋድ መዋቅራዊ ለውጥ ላይ ትኩረት አድርጎ ተከናውኗል። የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዳሉት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ መሪዎች በአዲስ አበባ የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ለመተግበር እንቅስቃሴ ጀምረዋል። በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ጥምር ኮሚቴዎች አቋቁመው ስራ መጀመራቸውም በአገሪቱ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ጉልህ አስተዋዕኦ አድርጓል። ይሁን እንጂ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሰብዓዊ ቀውስ በዘላዊነት ለመፍታት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በደቡብ ሱዳን የኢጋድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኢስማኤል ዋይስ በበኩላቸው በአገሪቱ አንጻራዊ ሰላም ቢሰፍንም 'አሁንም ብዙ መስራት ይገባል' ይላሉ። በመሪዎቹ መካከል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መልካም መሆናቸውን ገልጸው ለተግባራዊነታቸው ከዚህ በላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ ከኢጋድና ሌሎች አጋዥ አካላት ውጭ ሁለቱ ፓርቲዎች የአገሪቱን ወጣቶችና ሴቶች ማሳተፍና የጀመሩትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።  አል-ሸባብ በሶማሊያ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በመገታቱ በቀጠናው ኢኮኖሚው ለውጥ እየታየ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሶማሊያ የኢጋድ ልዩ መልዕክተኛ ሞሃመድ አሊ ጉዮ ናቸው። "በሶማሊያ ዜጎች በሰላም መንቀሳቀስ አይችሉም ነበር" ያሉት ቋሚ መልዕክተኛው አሁን በነጻነት መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ገልጸዋል። ሶማሊያ ከኢጋድና ከጎረቤት አገራት ጋር የጀመረችው ግንኙነት አሁን ላለችበት መነቃቃት ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል። በቀጣይም ዓለም አቀፍ የትብበር ተቋማት፣ ኢጋድና የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊያ መንግስትና ህዝብ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም