ቀጥታ፡

የሕዝብን ሃብት የመዘበሩና ሰብዓዊ መብት የጣሱትን ለሕግ የማቅረብ ሂደት ወደ ክልሎች መዘለቅ አለበት

አሶሳ ህዳር 7/2011 የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የጣሱና የሕዝብን ሃብት የመዘበሩ ግለሰቦችን ለሕግ ለማቅረብ የተጀመረው ሥራ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም እንዲተገበር የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹ  ለኢዜአ እንዳስታወቁት የፌዴሉ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የጣሱና የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የጣሉ ግለሰቦችን በመያዝ የጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ክልላቸው እንዲገባ ፍላጎታቸው ነው። ነዋሪዎቹ መንግሥት ተጠርጣሪዎቹን በማስረጃ አስደግፎ ለሕግ ለማቅረብ እያደረገው ያለው ጥረት እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ “ ግለሰቦቹ የፈጸሙት ወንጀል የአደባባይ ሚስጥር እየሆነ መጥቶ ነበር ” በማለት አስተያየታቸውን የሚጀምሩት አቶ ሙስጠፋ መሐመድ፣ ግለሰቦቹ የፈጸሙት ውንብድና ከወራሪው ጣሊያን ተግባር ባልተናነሰ አገርን አደጋ ላይ የጣለ ያህል ይሰማኛል ብለዋል፡፡ “የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሙስና እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ተፈጽሟል” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ የፌደራል መንግሥት የወሰደው እርምጃ ክልሉን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች በአፋጣኝ ሊወርድ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ እርምጃው አዲሶቹ ተሿሚዎች ከአድሏዊነት በጸዳ በህግና ህግ ላይ ብቻ ተመርኩዘው እንዲሰሩ ያስተምራል ብለዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሲራጅ ኤልያስ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) ደጋፊ ነህ ተብለው ከሱዳን ተይዘው መምጣታቸውንና ለስድስት ወራት ያለፍርድ መታሰራቸውን ይናገራሉ፡፡ በእስር ቤት ቆይታቸው ከተፈጸመባቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መካከል ጨለማ ቤት ታስረው ጥፍራቸውን በጉጠት መነቀልና ሌሎች ጭካኔ የተሞላበት ድርጊቶች እንደተፈጸሙባቸው ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ በተፈጠረው ለውጥ ከእስር ነጻ መውጣታቸውን የሚናገሩት  አቶ ሲራጅ፣“የሕዝብ አደራ በበሉ ግለሰቦች ላይ የተወሰደው እርምጃ በየቦታው ሲፈስ የነበረውን የሕዝብን እንባ ያበሰ ነው” ብለዋል፡፡ “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በመሰል ጥፋት ላይ የተሰማሩ አካላት ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው ” ሲሉም  ያሳስባሉ፡፡ ወጣት መመድ ዓሊ በበኩሉ “ግለሰበቦቹ በተለይ ህዝብ በቁጭት የጀመረውን የህዳሴ ግድብ ሃብት ማባከን ኢትዮጵያዊ ናቸው ለማለት ይቸግረኛል።ድርጊቱም አሳፋሪ ነው'' ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ በክልም መሰል ድርጊት ሊኖር ስለሚችል ጥናት ተደርጎ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በሙስናና ሰብዓዊ መብቶችን በጣሰ ድርጊት ተሰማርተዋል ያላቸውን ከ60 በላይ ሰዎች በዚህ ሳምንት ለሕግ ማቅረብ ጀምሯል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም