ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ጉባዔ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 ስምተኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ጉባዔ በተያዘው ወር አጋማሽ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች አዘጋጅቶ ላኪዎች ጋር በመሆን ህዳር 14 እና 15 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄደውን ጉባኤ የተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል። የሚኒስቴሩ የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አሰፋ ሙሉጌታ እንዳሉት ጉባዔው ከአገር ውስጥና ከተለያዩ አገራት በሚመጡ ተሳታፊዎች በተገኙበት በሸራተን አዲስ ሆቴል ይካሄዳል። ከ20 በላይ አገራት የሚመጡ 110 የውጭ አገር ገዥዎች፣ ከ200 በላይ የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች፣ ከ150 በላይ የመንግስት አመራሮች እንደሚሳተፉበትም ይጠበቃል። የንግድ ግንኙነትን ማጠናከር ዋነኛ ዓላማው የሆነው ጉባኤው የገበያ ትስስር መፍጠር፣ ዓለም አቀፍ ፍላጎትና አቅርቦትን ማወቅ፣ የመረጃና ለምድ ልውውጥ ማድረግ፣ የአገር ገጽታ መገንባትና የቱሪዝም ኮንፈረስን ማስፋት ያስችላል ተብሏል። በተያዘው ዓመት 532 ቶን የቅባትና ከ486 በላይ ቶን የጥራጥሬ እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ ከ819 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱንም አቶ አሰፋ ጠቁመዋል። ጉባዔው ይህን እቅድ ለማሳካት የራሱን አስተዋጾኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞችን አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ዮሐንስ እንደገለጹትም ባለፉት ሰባት ጉባዔዎች በተሰራው ስራ የተሳታፊዎች ቁጥር ጨምሯል፤ የዘርፉ ተዋንያንም የእቅዳቸው አካል እያደረጉት መጥተዋል። የዘንድሮውን ጉባዔም ነባር ደንበኞች ግንኙነታቸውን ያጠናክሩበታል፤ አዳዲሶች ደግሞ የዘርፉን እድሎችና አማራጮች እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል። በመሆኑም የማህበሩ አባላትም ሆኑ አባል ያልሆነ ማንኛውም ግለሰብ ምዝገባ በማካሄድ በጉባዔው መሳተፍ እንደሚችል አስታውቀዋል። በጉባዔው ከቻይና፣ ከሱዳን፣ ከተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች፣ ከጃፓን፣ ከህንድና ከሌሎች አገራት የሚመጡ ባለሃብቶች ዘርፉን የተመለከቱ  ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀርባሉ። "ስልታዊ የቢዝነስ ግንኙነትን ማጠናከርና ማሳደግ" የ8ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ጉባዔ መሪ ሃሳብ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም