የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፈው ወር 24 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፈው ወር 24 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፈው ወር ለመሰብሰብ ካቀደው 29 ቢሊዮን ብር ገቢ 24 ቢሊዮኑን ቢያሳካም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት ገለጸ። ሚኒስቴሩን ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር የሚለየውን መዋቅርን አፅድቆ የሰው ኃይል ድልድል እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል። ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ ከፍተኛ የግብር መሰብሰቢያ ወቅት በሆነው የጥቅምት ወር መሰብሰብ ካለበት 29 ቢሊዮን ብር 24 ቢሊዮን መሰብሰብ ተችሏል። በወሩ ገቢ አሰባሰብ የከፍተኛ ግብር ከፋዩና በአገር ውስጥ ገቢ 'ለውጥ የታየበት ነው' ያሉት ሚኒስትሯ ከገቢው አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው የአገር ውስጥ ገቢ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ በመቶ ቀናት እሰራዋለው ብሎ ባቀደው መሰረትም ከፍተኛ ግብር ከፋዩ ግብሩን ቶሎ አሳውቆ እንዲከፍል በመደረጉ የተሻለ ለውጥ ታይቷል ብለዋል። ሰራተኞቹ በፈረሙት ቻርተር ቅዳሜና እሁድ ጭምር በመግባት ለስራው መለወጥ 'የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ናቸው' ብለዋል። የመስሪያ ቤቱ አገልግሎት አሰጣጥ ችግርና የግብር ከፋዩ ታማኝ ሆኖ ግብሩን አለመክፈል ገቢው በታቀደው ልክ እንዳይሰበሰብ ምክንያት መሆናቸውንም ጠቁመዋል። በጥቅምት ወር ከግብር ማጭበርበር ጋር ተያይዞ ከኮንትሮባንድ ንግድ ወደ 123 ሚሊዮን ብር የሚገመት እቃ በቁጥጥር ስር ውሏል። በተቋሙ በኩል ያለውን ችግር ለማረም ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመግለፅ ግብር ከፋዩም በህጋዊ መንገድ በመስራትና የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል ሚኒስትሯ። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከተቻለ 'በእቅዱ መሰረት ገቢን ማሳካት ይቻላል' ብለዋል። በሌላ በኩል እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም የገቢዎች ሚኒስቴርር ኃላፊነት ከጉምሩክ የሚለየው መዋቅር ፀድቆ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል። የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ሚኒስቴሩ በዓመቱ ለመሰብሰብ ያሰበውን 213 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማሳካት የሚያስችሉ እንደሆኑም ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አስታውቀዋል።