የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ መሪዎች የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት መሻሻል እየታየበት ነው - ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ መሪዎች የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት መሻሻል እየታየበት ነው - ኢጋድ
አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ መሪዎች ባለፈው መስከረም የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት መሻሻል እየታየበት መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ገለጸ። የኢጋድ 66ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሂዷል። በዚህም የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም፣ በሶማሊያ ወቅታዊ ጉዳይና በኢጋድ መዋቅራዊ ለውጥ ላይ ውውይት አድርጓል። የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዳሉት፤ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል በነበረው አለመግባባት የተነሳ በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረው ሰቆቃና እንግልት ለጊዜውም ቢሆን መሻሻል አሳይቷል። በደቡብ ሱዳን አሁን ላለው ሰላም ኢጋድ ከፍተኛ ሚና እንደነበረውና በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ዶክተር ወርቅነህ ጠይቀዋል። ኢጋድ በሁለቱ ተቀናቃይ መሪዎች መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ አስፈላጊውን ድጋፍና ክተትል እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። በደቡብ ሱዳን የኢጋድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ኢስማኤል ዋይስ ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ሁለቱ ተቀናቃኝ መሪዎች በአዲስ አበባ የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። በፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር አደራዳሪነት በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም፣ እንዲሁም በጁባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። ''በዚህም በደቡብ ሱዳን የዜጎች መፈናቀል፣ እንግልትና ግድያ ቆሟል፤ አሁን በደቡብ ሱዳን አንጻራዊ የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል'' ብለዋል። በሶማሊያ የኢጋድ ልዩ መልዕክተኛ ሞሃመድ አሊ ጉዮ በበኩላቸው አል-ሻባብ በሶማሊያ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በመገታቱ በቀጠናው ኢኮኖሚው ለውጥ እያሳየ መምጣቱን ገልጸዋል። የኢጋድ መዋቅራዊ ማሻሻያም በዝግ ስብሰባ ውውይት እየተደረገበት ነው።