ጥያቄው ምላሽ ማግኘቱ ህዝቡ ችግሮቹን በቅርበት ለመፍታት ያስችላል --- የጎፋ ዞን ተወላጆች አስተያየት

አርባምንጭ ህዳር 7/2011 የመዋቅር ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት ለመፍታት እንደሚያስችል አስተያየታቸውን የሰጡ የጎፋ ዞን ተወላጆች ገለጹ፡፡ አዲሱ መዋቅር የህዝቡ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡ ከጎፋ ተወላጅ መካከል ወይዘሮ  አማረች በየነ  ለኢዜአ እንዳሉት በተለያየ ምክንያት የህዝቡ የዞንና የወረዳ መዋቅር ጥያቄ ምላሽ ሳያገኙ በመቆየቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሆኖበታል፡፡ በቅርቡ የክልሉ ምክር ቤት የጎፋ ዞን ጥያቄ መመለሱ  ለመልማትም ሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በቅርበት ምላሽ ለማግኘት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ የአከባቢው ወጣቶች የተሻላ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም  ጠቁመዋል፡፡ ከግብር ጋር በተያያዘ ለፈቃድ፣ ለጣት አሻራና ለሂሳብ ሪፖርት መሎ ኮዛ ወረዳ ያለ አንድ ነጋዴ አርባ ምንጭ ለመድረስ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ለመጓዝ እንደሚገደድ የተናገሩት ደግሞ አቶ ነፃነት ገመዳ ናቸው፡፡ የጎፋ ዞን መሆን ለዘመናት ሲንገላቱ የነበሩ ነጋዴዎችን ከጊዜ፣ ከጉልበትና ከገንዘብ ወጪ እንደሚታደግ ገልጸዋል፡፡ በፈዴራል ስርዓቱ መሠረት በተዋረድ የተዘረጋው የስልጣን እርከን የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡ የደንባ ጎፋ ወረዳ ነዋሪው  አቶ ኢያሱ ጣሰው  በበኩላቸው የቀድሞው የጋሞ ጎፋ ዞን ቆዳ ስፋቱ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ በርካታ የመሠረተ ልማት ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የጎፋ ዞን መዋቅሩ የመሠረተ ልማትና ሌሎችንም  ችግሮችን ለመፍታት  እንደሚበጅ  አስረድተዋል፡፡ "አከባቢው እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጤፍ፣ ኮሮሪማ፤ ሌጦና የመሳሰሉ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶችን በስፋት የሚያመርት በመሆኑ በዘርፉ ያለውን የንግድ ትስስር ሰንሰለቱን በማሳጠር የአርሶ አደሩንም ሆነ የነጋዴዎችን ተጠቃሚነት ያሳድጋልም" ብለዋል፡፡ ወይዘሮ ንግስት ተፈራ  በፌዴራልና በክልል መንግስት የሚሠሩ የመንገድ  ፕሮጀክቶች በክትትል ማነስ ምክንያት በጊዜ አለመጠናቀቃቸው ችግር ሲፈጥር መቆየቱን አመልክተዋል፡፡ ለአካባቢው የዞን መዋቅር መፈቀዱ እነዚህ ችግሮች ተከታትሎ በመፍታትና በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ይታይ የነበረውን ችግር ለመፍታት በባለቤትነት እንዲሰራ ያስችላል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ በልማትና በመልካም አስተዳደር እጦት ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን ቅሬታ ለመፍታት ያግዛል ብለዋል፡፡ የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቻውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ቀድሞ በጋሞ ጎፋ ስር የነበረው አዲሱ የጎፋ ዞን ሰባት ወረዳዎችንና ሁለት የከተማ አስተዳደሮችን በማቀፍ መዋቀሩን በቅርቡ ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም