ቀጥታ፡

የኢንዶኔዢያው ኩባንያ በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ ለመሰማራት ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ ህዳር 7/2011 ሱንጋይ የተሰኘ የኢንዶኔዢያ ኩባንያ በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ እድሎችን ለመጠቀም መዘጋጀቱን ገለጸ። በኢንዶኔዢያ፣ ማሌዢያና ሲንጋፖር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ ሱናጋይ ቡዲ ግሩፕ ከተሰኘ የግብርና ምርቶች አቀናባሪ የቢዝነስ ስብስብ ኃላፊ ሳንቶሶ ዊናታ ጋር ተወያይተዋል። አምባሳደሩ የኢንዶኔዢያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ አትራፊ የቢዝነስ አቅሞችን እንዲጠቀሙባቸው ጠይቀዋል። የቢዝነስ ስብስቡ የአገሪቷን የንግድና የኢንቨስትመንት እድሎች ተጠቅሞ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ ቢሰማራ ትርፋማ እንደሚሆንና የዘርፉን እሴት እንደሚጨምር መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የስብስቡ ኃላፊ ሳንቶሶ ዊናታ በበኩላቸው ስብስቡ በኢትዮጵያ የሚገኙትን እድሎች ለመጠቀም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። አምባሳደሩ በተመሳሳይ ከኢንዶኔዢያ የሳይንስ ተቋም ኃላፊ ዶክተር ውሪያንድሪ እና ከከፍተኛ ተመራማሪዎች ጋር ተወያይተዋል። አምባሳደሩ የደቡብ-ደቡብ ትብብር በሁሉም መስክ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው የጥናትና ምርምር ትብብርም የዚሁ አካል ተደርጎ ሊሰራበት እንደሚገባ አመልክተዋል። ተቋሙና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ተጎዳኝተው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና አጋርነታቸውን እንዲያጎለብቱም ጠይቀዋል። ዶክተር ውሪያንዲሪም ተቋሙ ከኢትዮጵያ የጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንደሆነ ገልጸውላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም