ቀጥታ፡

ኢህአዴግ ምግባረ ብልሹ አመራሮችን ለፍርድ ለማቅረብ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው-ዶክተር ዲማ ኖጎ

አዲስ አበባ ህዳር 6/2011  የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ውስጡን በመፈተሽ ምግባረ ብልሹ አመራሮችን ለፍርድ ለማቅረብ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ዲማ ኖጎ ተናገሩ። በሀብት ምዝበራና በዜጎች መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር "ወንጀል ሰርቶ የትም ማምለጥ እንደማይቻል ትምህርት የሰጠ" መሆኑንም አክለዋል። የፌደራል አቃቤ ህግ በቅርቡ ይፋ ባደረገውና  አምስት ወራትን ወስዶብኛል ባለው ምርመራው "63 የመንግስት ሹማምንቶችን በአገር ሃብት ምዝበራና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ጠርጥሬያቸዋለሁ " ማለቱ የሚታወስ ነው። ይህን ተከትሎም የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሃላፊ ሜጄር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በርካታ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ኢዜአ ጉዳዩን አስመልክቶ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ዲማ ኖጎ ጋር ቆይታ አድርጓል። ምክትል ሊቀመንበሩ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አንድ ስርዓት ተገርስሶ ተተኪው መንግስት የቀድሞ ስርዓት ኃላፊዎችን "ፍትህ ባጓደለ ክስ" ተጠያቂ ሲያደርግ ይስተዋላል ። አሁን ላይ ከዚህ በተለየ ስርዓቱ ሳይለወጥ  የመንግስት ሹማምንቶች በህግ ጥላ ስር እየዋሉ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ)  በዚህ ረገድ እያሳየ ያለውን ለወጥ አድንቀዋል። ባለፉት 27 ዓመታት በተደራጀ መልኩ ሰብዓዊ መብትን ሲጥሱና የህዝብን ሀብት ሲዘርፉ የነበሩ "የመንግስት ኃላፊዎች በርካታ ናቸው" ያሉት ዶክተር ዲማ፤ በቀጣይ በመሰል ተግባር ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች ደረጃ በደረጃ ለህግ እንደሚቀርቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ጠቅላይ  ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሃላፊነት ሲመጡ ፍትህን ለማስፈን በትኩረት እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን አስታውሰው፤ ቃላቸውን ለመጠበቅ እየወሰዱት ላለው ተግባር አድናቆት ችረዋል። የተደረገው ዝርፊያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣ  የወንጀል ድርጊት መሆኑንም ተናግረዋል ዶክተር ዲማ። እየተከናወነ ያለውን ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉን ተግባርም "ምንም አይነት ሰበብ ፈጥሮ ማንም የትም  መደበቅ እንደማይችል ትምህርት የሰጠ መሆኑንም" አውስተዋል። በተጠርጣሪነት የተያዙ ሰዎች ሰብዓዊ መብታቸው  ሳይጓደል ለፍርድ ማቅረብ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) መንግስት ለውጡን ለማስቀጠል ውጭ ላሉ የፖለቲካ ኃይሎች ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በቅርቡ ወደ አገር ቤት የገባ የፖለቲካ ድርጀት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም