ቀጥታ፡

የክልሉ ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ አባላት ሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

ጅግጅጋ ህዳር 6/2011 የሶማሌ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና ፖሊስ አባላት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች በማክበርና በማስከበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስገነዘበ፡፡ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ፖሊስ ኮሚሽን አመራርና አባላት እንዲሁም ሌሎች የጸጥታ አካላት የተሳተፉበት በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና ትናንት በጅግጅጋ ከተማ ተጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቱ ገብሬ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችና በሕገ መንግሥት በግልጽ የተቀመጡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የክልሉ ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል፡፡ የፖሊስ አባላት በሕግ ጥላ ሥር ለሚገኙ ተጠርጣሪዎችና ወንጀለኞች በሃይማኖትም ሆነ በሕግ የተሰጣቸውን ክብር በመጠበቅ የጤና ፣ የምግብ፣ የንጹህ መኝታ አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም በቤተሰባቸው እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባል ብለዋል። የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታቸውን በሚገባ አውቀው እንዲያከብሩና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ ሰልጣኞች በቆይታቸው የሰብዓዊ መብቶች ምንነት፣ የታራሚዎች አያያዝ፣ ሰብዓዊ መብትን ያማከለ አሰራር ለልማት፣ ሰብዓዊ መብቶች በማክበርና ማስከበር የማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ አመራር ሚና፣ የዜጎች መብት ለመጠበቅ የዜጎችና የመንግሥት ሚና በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያዘጋጀውና ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ስልጠና ላይ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ፖሊስ  እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት፣ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም