ኢህአዴግ በአመራር ዘመኑ ህዝቡን ለቅሬታና ምሬት የዳረጉ ጥፋቶች እንደተፈጸሙ መገንዘቡን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢህአዴግ በአመራር ዘመኑ ህዝቡን ለቅሬታና ምሬት የዳረጉ ጥፋቶች እንደተፈጸሙ መገንዘቡን አስታወቀ
አዲስ አበባ ህዳር 5/2011 በአመራር ዘመኑ ህዝብና የህዝብ አደረጃጀቶችን ለቅሬታና ምሬት የዳረጉ ጥፋቶች እንደተፈጸሙ አበክሮ የሚገነዘብ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ለተከታታይ ዓመታት የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችን በማካሄድ የችግሮቹን ምንጭና መፍትሄዎች ለመለየት ሲሰራ የቆየው ከዚሁ በመነሳት እንደሆነም ገልጿል። "ድርጅታችን ቁልፍ የሆነው ችግር መንግስታዊና የፓርቲ ስልጣንን ለኀብረተሰባዊ ለውጥ ከማዋል ይልቅ የግል ጥቅምን ለማካበት የማዋል ፍላጎትና ተግባር መሆኑን በጥልቅ ተሃድሶው ግምገማ መለየቱ ይታወሳል" ብሏል። አሁን ከተደረሰበት ለውጥ በመነሳት የህዝብ ቅሬታ ምላሽ ሳያገኝ እንዲቆይ ማድረግ የሚቻልበት አንዳችም መንገድ እንደሌለ የተረዳው ድርጅቱ ለህዝቡ በገባው ቃል መሠረት ስር ነቀል የአመራርና የአሰራር ለውጥና ማሻሻያዎች ማድረጉን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል። "የለውጥ ጊዜው አጭር ቢሆንም በስፋቱና በጥልቀቱ በአገሪቱ ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው" ያለው የግንባሩ ጽህፈት ቤት፤ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ዘላቂነት ከማረጋገጥ ጎን ለውጡ ተቋማዊ እንዲሆን ማድረግ የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት በድርጅቱ እየተፈጸመ ያለ ተግባር እንደሆነም አመልክቷል። ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታና እሮሮ ከሚሰማባቸው መካከል የፍትህ ስርዓቱ በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሌብነትና ብልሹ አሰራር ሊያስቆም አለመቻሉ እንደሆነም ጠቁሟል። "የዘርፉ ዋነኛ ተልዕኮ ህገ ወጥነትን መከላከልና ሲፈፀምም ህጉን ተከትሎ የእርምት እርምጃ መውሰድ ቢሆንም በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የተደራጁ ኃይሎች በተሰጣቸው ኃላፊነት ልክ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ከማስቆም ይልቅ ራሳቸውን የህገ ወጦች ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሳሪያ በማድረግ በአገርና በህዝቦች ላይ በደል ሲፈፅሙ ቆይተዋል" ብሏል። የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚጎዱ አሻጥሮች ሲፈፀሙ፣ የዜጎችና የቡድኖች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በገሃድ ሲጣሱ እንዲሁም መንግስታዊ ስልጣን ለሽብር ተግባር ማስፈፀሚያ ሲውል መቆየቱንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። ከዚህ በመነሳት ድርጅቱና መንግስት በዚህ ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ በማመን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በርካታ ጥናት ሲያደርጉና እርምጃዎችን ሲወሰዱ መቆየታቸውን ጠቁሟል። በቅርቡም የተሰጣቸውን መንግስታዊና ህዝባዊ ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ በአስከፊ የምዝበራ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሽብር ተግባር በመሳተፋቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በህጋዊ መንገድ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ብሏል። ከድርጅቱ ህዝባዊ ባህሪ በማይመነጭና ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዓላማዎች ፍፁም በተፃራሪ ድርጊቶች የተሰማሩ ግለሰቦችንና ግብረ አበሮቻቸውን በህግ ቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የግንባሩ ጽህፈት ቤት በላከው መግለጫ አስታውቋል። መላ የድርጅቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የአገሪቱ ህዝቦች የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ከመንግስት ጎን በመቆም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ኢህአዴግ ጥሪ አስተላለፏል።