የህንጻዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያ እጥረት ተሽከርካሪዎችን መንገድ ላይ ለማቆም እያስገደደ ነው - ጥናት - ኢዜአ አማርኛ
የህንጻዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያ እጥረት ተሽከርካሪዎችን መንገድ ላይ ለማቆም እያስገደደ ነው - ጥናት
አዲስ አበባ ህዳር 5/2011 በህንጻዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያ እጥረት ሳቢያ 70 በመቶ ያህሉ ተገልጋዮች መኪናቸውን መንገድ ላይ ለማቆም እንደሚገደዱ አንድ ጥናት አመለከተ። የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህንጻ ግንባታና ኪነ ህንጻ ትምህርት ክፍል የህንጻዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎች ላይ ባካሄደው ጥናት ዙሪያ ተወያይቷል። በጥናቱ ከተካተቱ የመዲናዋ 167 ህንጻዎች መካከል 84 በመቶዎቹ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቢኖራቸውም በውስጣቸው ከሚገኙ ተቋማት ተሽከርካሪዎች ሌላ ለተገልጋዮችና ጎብኚዎች በቂ የማቆሚያ ስፍራ የላቸውም። የተሽከርካሪ ማቆሚያ ችግሩ በግል ተቋማት ብቻ ሳይሆን ከግንባታ ፍቃድና ከመሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚሰሩ የመንግስት ተቋማት ላይም ይስተዋላል። አንዳንድ ህንጻዎችም ለተሽከርካሪ ማቆሚያዎች ተብለው የተዘጋጁ ስፍራዎችን ለንግድ አገልግሎት እየተጠቀሙበት እንደሚገኙም ጥናቱ ጠቁሟል። ይህ ደግሞ አብዛኞቹን ተገልጋዮችና ጎብኚዎች ተሽከርካሪዎቻቸውን የመኪናና የእግረኛ መንገዶች ላይ እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል። በተጨማሪም በትራፊክ ፍሰት፣ በእግረኞች ደህንነትና በመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ በመሬት አጠቃቀም ጭምር አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንዳለውም ጥናቱ ጠቁሟል። የህንጻዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ እጥረቱ ምክንያቶች መካከል የህንጻ ኮድ ህግ አፈጻጸምና ክትትል ድክመት መኖር፣ የግንባታ ባለሙያዎች ህግና ሙያዊ ስነ ምግባር ጠብቆ አለመስራትና የህንጻ ባለቤቶች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ፍለጋ ተጠቅሰዋል። የህንጻ ባለቤቶችና ባለሙያዎች የህንጻዎች ደረጃ መመሪያና ህጎች ላይ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት ደካማነትም እንዲሁ። ጥናቱ እንደሚያመላክተው በመዲናዋ የህንጻዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እጥረቱ ብቻ ሳይሆን ማቆሚያ ያላቸውም ጉድለቶች ይስተዋልባቸዋል። የተሽከርካሪዎች መግቢያና መውጫን ያለመለየት፣ ወደ ማቆሚያዎቹ የሚያሳዩና የአካል ጉዳተኞች ምልክቶች፣ የፍጥነት መገደቢያ፣ በቂ ብርሃንና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አለመኖር እንዲሁም አንሸራታች ወለል በጥናቱ እንደ ችግር ታይቷል። የተሽከርካሪ ማቆሚያ (የፓርኪንግ) ፖሊሲ በሌሎች መመሪያዎች ውስጥ ተካቶ ሳይሆን ራሱን ችሎ መተግበር ጥናቱ ካስቀመጣቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎች መካከል ይጠቀሳል። በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ ያለውን የተሽከርካሪ ማቆሚያ መመሪያ ማሻሻል፣ የትራንስፖርት ፖሊሲውን እግረኛ ተኮር ማድረግ፣ የግሉ ዘርፍ በፓርኪንግ ዘርፍ እንዲሰማራ የማበረታት ተገቢነትም ተገልጿል። የህንጻ ግንባታና ዲዛይን ቁጥጥር ባለስልጣንን መዋቅራዊ አደረጃጃት ማጠናከርና የሰው ኃይል ማሟላትና የባለድርሻ ተቋማትን የኃላፊነት መደራረብና የቅንጅት ማነስ ችግሮችን መፍታት አስፈላጊነትም በጥናቱ ተጠቁሟል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም ከተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎች ጋር በተያያዘ ጥናቶች ቢካሄዱም የአፈጻጻም ክፍተቱን ማረም እንደሚገባ ተናግረዋል። ከፍተኛ ገንዘብ የማይጠይቁና ጥራታቸውን የጠበቁ ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ እንዲውሉ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል። የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂረኛ ሂርጳ በበኩላቸው የተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንዲደረግ 'እንሰራለን' ብለዋል። የህንጻዎችን የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎች ለንግድ እንቅስቃሴ ያዋሉ ተቋማት በህግ እንዲጠየቁ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።