ኢትዮጵያ ለኤርትራ ሕዝቦችና መንግስት የ"እንኳን ደስያላችሁ" መልዕክት አስተላለፈች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለኤርትራ ሕዝቦችና መንግስት የ"እንኳን ደስያላችሁ" መልዕክት አስተላለፈች
አዲስ አበባ ህዳር 5/2011 በኤርትራ ላይ ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ በመነሳቱ ለኤርትራ ሕዝቦችና መንግስት "እንኳን ደስያላችሁ" በማለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የደስታ መልዕክት አስተላለፈ። የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ዛሬ አንሰቷል። 15 አባላት ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀቡን ለማንሳት ባለፈው ሰኞ በደረሰበት ስምምነት መሰረት ነው ማዕቀቡ ዛሬ የተነሳው። የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት፤ በኤርትራ ላይ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ጥሎት የቆየውን ማዕቀብ እንዲነሳ የኢትዮጵያ መንግስት ላቀረበው ጥያቄ ተመድ ለሰጠው አዎንታዊ ምላሽ ምስጋና አቅርቧል። ለዚህ ማዕቀብ መነሳት የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል አገሮች በቀጣናው ለሚካሄድ የጋራ ጥቅም መሰረት ላደረጉ ለውጦች ላሳዩት ትብብርም መንግስት አድናቆቱን ገልጿል። የማዕቀቡ መነሳት በአፍሪካ ቀንድ ለሚታየው መረጋጋትና ዘላቂ ሰላም መፈጠርና በቀጣናው አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል። ውሳኔው በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በአዲስ መልከ የተጀመረው የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ትስስር ቱሩፋት እንደሚያበለጽገው ነው ያመለከተው። ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም፣ ልማት ትብብር ከኤርትራና ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር አብራ ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነትንም ጽህፈት ቤቱ አረጋግጧል። ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ከኤርትራ ጋር የተፈረመው የሰላም ስምምነትና ኤርትራ ከጅቡቲ ጋር የደረሰችበት በጋራ የመስራት ስምምነት ለማዕቀቡ መነሳት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጹት፤ የማዕቀቡ መነሳት "ለኤርትራ ብዙ አማራጮችን ይዞላት ይመጣል" በተለይ የውጭ ባለሐብቶችን በመሳብ አስመራን ወደ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይቀላቅላታል። ውሳኔው ለቀጣናው አገሮች ህዝቦች የሚሰጠውን ጠቀሜታ ለመመልከት እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ "በተመሳሳይ ያሉብንን ችግሮችና ፈተናዎች እንዴት መፍታት እንደምንችል የምንመለከትበት ነው" ሲሉ አምባሳደር ታዬ ገልጸዋል።