ኢትዮጵያ ለተመድ መጠናከር የበኩሏን ድርሻ ትወጣለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለተመድ መጠናከር የበኩሏን ድርሻ ትወጣለች
አዲስ አበባ ህዳር 5/2011 ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) መጠናከር የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣ ገለጸች፡፡ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ ለጽህፈት ቤቱ ባደረጉት ንግግር፣ ''የሰላም እና ደህንነት ችግር ዓለም አቀፋዊ ስጋት እንደሆነና ለችግሩ የጋራ ምላሽ ለመስጠት ከባለብዙ ወገን እንቅስቃሴ የተሻለ አማራጭ የለም'' ብለዋል፡፡ ተመድ ከስኬቶቹ በመማር ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡ ዓለም የተጋረጠበትን ሰብዓዊ ስጋቶችን በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንዴት መፍታትና ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል መነጋገር እንደሚገባ አመልክተዋል። የተመድ የተቀናጀ የደህንነት ስርዓት የጦርነትን አደጋ ለመቀነስ እንደሚረዳ ጥርጥር የሌለው መሆኑን በመጥቀስ ለብዙ ዓመታት ያህል ሰላም በማስከበሩ በኩል በተመድ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አውስተዋል፡፡ በርካታ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ የአሸባሪነትና የአክራሪነት ስጋቶች እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በዓለም የሰላም ስጋት እንዲጨምር ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ ድህነት፣ የበሽታ መስፋፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለአለማችን ደንቃራ የሆኑ የደህንነትና የሰብዓዊ ችግሮች ዋነኛ መንስኤ መሆናቸውን በመጥቀስ እነዚህን ለማስወገድ ተመድ ከመቼውም ጊዜ በላይ መስራት እንደሚጠበቅበት አውስተዋል። የተመድ ቻርተር፣ የጸጥታው ምክር ቤት ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲችል በርካታ አማራጮች የተቀመጡበት መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፣ ግጭቶች ከመቀስቀሳቸው በፊት የመከላከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከ70 ዓመታት በላይ ለተመድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገችው ሁሉ አሁንም ለድርጅቱ መጠናከር የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አስምረውበታል፡፡