የንግድ ቤቶች ኪራይ ተመን ማሻሻያ በመጪው ወር ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
የንግድ ቤቶች ኪራይ ተመን ማሻሻያ በመጪው ወር ይደረጋል
አዲስ አበባ ህዳር 5/2011 የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው የኪራይ ንግድ ቤቶች ላይ የተመን ማሻሻያ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ እንደሚያደርግ አስታወቀ። ኮርፖሬሽኑ አዲስ የሚተገብረውን የኪራይ ተመን አስመልክቶ በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በዚህ ጊዜ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ረሻድ ከማል እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው የኪራይ ንግድ ቤቶች ላይ የተመን ማሻሻያ የከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ለማድረግ የዳሰሳ ጥናትና ሶፍት ዌር ማበልጸግ ዝግጅት አድርጓል። የኪራይ ማሻሻያው ኮፖሬሽኑ እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኋላ አስተዳደራዊና የልማት ወጪዎችን በራሱ ለመሸፈን፣ በንግድ ቤቶቹ መካከል የተለያዩ የኪራይ ተመን እየተተገበረ በመሆኑ የተፈጠረውን ቅሬታ ለመፍታትና ፍትሃዊ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል። በተለይም በግልና በመንግስት የቤቶች ኪራይ ተመን ጋር ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማቀራረብ፣ ተጨማሪ ቤቶችን ገንብቶ ለተጠቃሚ ለማከራየት፣ የቤት የኪራይ ተመን የአስተዳደር መዘበራረቅን ለመቅረፍ መሆኑንም ገልጸዋል። ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከየሚያስተደድራቸው 18 ሺህ 153 ቤቶች መካከል 6ሺህ 635 ቤቶች የንግድ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ በንግድ ቤቶቹ የኪራይ ተመን ማሻሻያ ለማድረግ መስፈርት ወጥቷል። የኪራይ ተመኑ ቤቶቹ የሚገኙበት አካባቢ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ፣ የቦታ ደረጃና የካሬ ሜትር ስፋት መስፈርት መሰረት ማድረጉን ተናግረው ተመኑ ከ30 ካሬ ሜትር በላይ ለሆኑ ቤቶች ከ15 በመቶ እስከ 85 በመቶ ድረስ በየደረጃው ተቀናናሽ የሚያደርግ አሰራርን ይከተላል። የኪራይ ማሻሻያው ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት ሰፊ የግንዛቤ ማሰጨበጫ ሥራ፣ ስለ ኪራይ ተመኑ በቂ ማብራሪያና ተከራዮቹ ያላቸው ቅሬታ ከተፈታ በኋላ ነው ወደተግባር የሚገባው ሲሉ አብራርተዋል። በመሆኑም ተከራዩ ማህበረሰብ ይህን ተገንዝቦ እራሱን ከአላስፈላጊ ውዥንብሮች በመራቅ ያሉትን ጥያቄዎች ሁሉ ለኮርፖሬሽኑ ማቅረብ እንደሚችል አቶ ረሻድ ተናግረዋል። የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶችን የመንግስት ለማድረግና የወጣውን አዋጅ ቁጥር 47/67 ተከትሎ በተለያዩ ስያሜ ሲሰራ የነበረው ተቋሙ በ2009 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 398/2009 እንደ አዲስ የተደራጀ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው።