ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የብራዚል አምባሳደር አሰናበቱ

አዲስ አበባ ህዳር 5/2011 ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር አሰናበቱ። ፕሬዝዳንቷ በጽህፈት ቤታቸው ከአምባሳደር ኦክታቪዎ ሄንሪክ ኮርቴስን ጋር በነበራቸው ቆይታ ብራዚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል። በተለይም በሁለቱ አገራት መካከል ያሉ የልማት ትብብር ስምምነቶች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ እና የሁለቱ አገራት ጠንካራ ግንኙነት በአዲስ ተተኪ አምባሳደር እንዴት ማስቀጠል ይቻላል? በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር በግብርና፣ በሃይል አቅርቦት እና በስኳር ኢንዱስትሪ መስኮች ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በኢንቨስትመንት ዘርፍም ማሳደግ እንደምትሻ ለአምባሳደሩ መግለፃቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት የፕሮቶኮልና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ተናግረዋል። አምባሳደር ኦክታቪዎ በበኩላቸው በነበራቸው የሶስት ዓመታት ቆይታ የኢትዮጵያና የብራዚልን ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ከነበረው በላይ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት የገለፁት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ብራዚል የሚያደርገው የቀጥታ በረራ ግንኙነቱን የበለጠ የማሻሻል ዕድል እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት። እሳቸውን ተክተው የሚመጡት አምባሳደርም የሁለቱን አገራት ትብብር የበለጠ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ለነበራቸው ቆይታ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ለሁለቱ አገራት ሰላምንና ብልጽግናን ተመኝተዋል። ብራዚል ኤምባሲዋን አዲስ አበባ ከከፈተች እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2005 ወዲህ ኦክታቪዎ ሄንሪክ ኮርቴስ በኢትዮጵያ ሶስተኛው አምባሳደር ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም