መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የጀመረው ሥራ እንዲጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን... የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የጀመረው ሥራ እንዲጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን... የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች
ሰመራ ህዳር 5/2011 መንግስት የሀገርን ሃብት የመዘበሩና የዜጎችን ሰብአዊ መብት የጣሱ ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። በሰመራ ከተማ የሚኖሩት አቶ መሃመድ ሃሚድ ብዙ ዜጎች በአስከፊ ድህነት ውስጥ በሚኖሩባት ሀገር በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ለግለሰቦች የግል ጥቅም መመዝበሩ እንዳሳዘናቸውና ታሪክ የማይረሳው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። "በኢፌድሪ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪን ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ አመራሮች ተፈጸመ የተባለው ምዝበራ በሀገራችን የሙስና ወንጀል ምንያክል አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱንና የህግ የበላይነትም በግለሰቦች ተጽዕኖ ስር መውደቁን በተጨባጭ ያሳየ ነው" ብለዋል። በወንጀሉ የተዘፈቁ ሙሰኞችንም ሆነ የሰው ልጅን ክብር በማናለብኝነት ከባህልና ሃይማኖታዊ እሴቶቻ በሚጻረር መልኩ በዜጎች ላይ አላግባብ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን መንግስት ለህግ ለማቅረብ የጀመረው ስራ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል። "እነዚህ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወንጀለኞች በየክልሉና ወረዳዎችም ጭምር ያሉ በመሆኑ መንግስት አስከታችኛው እርክን ድረስ ወርዶ ለፍርድ ማቅረብ ይኖርበታል" ሲሉ ጠቁመዋል። ለዚህም እንደዜጋ ወንጀለኞችን በመጠቆምና በማጋላጥ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። በሎግያ ከተማ የሚኖረው ወጣት ኑሩ ሰኢድ በበኩሉ "ባለፉት ዓመታት በተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች አብዛኛው የአገሪቱ ዜጎች የእለት ጉርስን ለማገኘት ሲቸገሩ ጥቂት የመንግስት ሹማምንት የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩባት ሀገር ተፈጥሯል" ብለዋል። ሀገርና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ወደጎን ትተው የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሯሯጡና የሰዎችን ሰብአዊ ክብር ሲጥሱ በነበሩ ግለሰቦች ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ የህግ የበላይትና የተጠያቂነት አሰራርን የሚያሰፍን በመሆኑ ከመንግስት ጎን አንደሚቆም ተናግሯል። ወጣት ኑሩ እንዳለው በህገወጦች ሲፈጸሙ በነበሩ ህገወጥ ተግባራትና ሙስና ሕብረተሰቡ በሀገሪቱ የፍትህ ተቋማት ላይ ያለው እምነት እየተሸረሸር እንዲመጣ አድርጓል። "በአሁኑ ወቅት መንግስት እየወሰዳ ያለው እርምጃ በተለይም ለቀጣዩ ትውልድ ማንም ሰው ከህግ በላይ አንዳልሆነ ያስተምራል" ብሏል። የሎግያ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰአዳ ጀማል በበኩላቸው "ከድሃ አገርና ህዝብ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘበው ከአንድ ተቋም ሲዘረፍ ሙሰኞቹ ብቻ ሳይሆኑ አይተው አንዳላዩ ሲያልፉ የነበሩ ባለስልጣናትም ሊጠየቁ " ይገባል ብለዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ህዝቦች የሕዳሴውን ግድብ ለመደገፍ ከእለት ጉርሳቸው ቀንሰው ያዋጡትን ገንዘብ አለአግባብ ለግል ጥቅም መመዘብር በሀገርና ህዝብ ላይ የተፈጸመ ከፍተኛ ክህደት መሆኑንም ተናግረዋል። በሜቴክ የተፈጸመው ድርጊት ሌሎች በውጤታማነታቸው የሚሞካሹ ትልልቅ የመንግስት የልማት ድርጅቶችም በሙሰኞች ይመዘበሩ ይሆናል የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬና ስጋት እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል። በመሆኑም መንግስት የጀመረውን የሀገርን ሃብት የማስመለስና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲዊ ክብር የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት የጀመረው ሥራ የበለጠ እንዲጠናከር ጠይቀዋል። ጅማሮው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የሁሉም ዜጋ ንቁ ተሳትፎ የሚያስፈልገው በመሆኑ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።