ቀጥታ፡

መንግስት የወሰደው እርምጃ የፍትህ ስርዓቱ ህዝባዊ አመኔታን ያጎለብታል - በጎንደር አስተያየት ሰጪዎች

ጎንደር/ደብረ ብርሃን ህዳር  5/2011 በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሌብነት ወንጀል በተሳተፉ ተጠርጣሪዎች ላይ መንግስት የወሰደው እርምጃ የፍትህ ስርዓቱ ህዝባዊ አመኔታ እንደሚያጎለብት በጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የመንግስትን እርምጃ እንደሚደግፉ በደብረ ብርሃን ከተማ  ወጣቶችም ተናግረዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት በተጠርጣሪዎች ላይ መንግስት የወሰደው እርምጃ ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚኖረውን አመኔታ የሚያሳድግ ነው፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አድማስ ደሞዜ በሰጡት አስተያየት መንግስት በከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ላይ መወሰድ የጀመረው እርምጃ የህግ የበላይነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ " የህዝብን አመኔታ ባጎደሉ ጥቂት ግለሰቦች ከፍተኛ የሀገር ሀብት መመዝበሩ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው"  ያሉት አቶ አድማሴ እርምጃው  ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የፍትህ ስርዓቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ህዝባዊ አመኔታው እንዲጨምር እርምጃው በክልሎች ጭምር መቀጠል አለበት ያለው በአማራ ወጣቶች ማህበር የጎንደር ከተማ ወጣቶች ማህበር ሊቀ-መንበር ወጣት ይሁኔ ዳኘው ነው፡፡ በሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለተቀጣጠለው የለውጥ ማዕበል ወጣቱ ግንባር ቀደም ተጋድሎ ማድረጉን ያስታወሰው ወጣቱ፤ ስልጣንን ተገን አድርገው ምዝበራ የፈጸሙ አካላት ከህግ እንደማያመልጡ በተጨባጭ እየተወሰደ ያለው  እርምጃ ማሳያ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በከተማው በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት ሃምሳ አለቃ አበበ መንግስቴ እንዳሉት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ መነሻ በማድረግ ምዝበራና  የሰብአዊ መብት ጥሰት በፈጸሙ የስራ ኃላፊዎች መረጃ በማሰባሰብ የተወሰደው እርምጃ ለህግ የበላይነት መጠናከር አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነው፡፡ የጎንደር ከተማ የሰላምና የልማት ኮሚቴ ሰብሳቢና የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ባዩ በዛብህ  ሙስና በመፈጸሙ ባለስልጣናት መንግስት የወሰደው እርምጃ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ "በዚች ደሃ ሀገር በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዝብ በግለሰቦች መመዝበሩ በስልጣን ላይ የነበሩ ግለሰቦች ለሀገር አሳቢ አለመሆናቸውን ያመላክታል" ያሉት አቶ ባዩ ለህግ የበላይነት መስፈን የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማት ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ መንግስት በተጨባጭ መረጃ ተደግፎ ለህዝብ ይፋ ያደረገው የባለስልጣኖች ምዝበራና የሰብአዊ መብት ጥሰት ወደፊትም ግልጽነትን በተላበሰ የህግ አሰራር መቀጠል እንደሚኖርበት የሀገር ሽማግሌው ተናግረዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ የህዝብ ስልጣንን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይቻል አመላካች በመሆኑ ለአዲስ ተሿሚዎች ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ለህግ የማቅረብ ስራን እንደሚደግፉ በደብረብርሃን ከተማ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡   ወጣት አዲስ አሰግድ  እንደገለጸው  የተፈጸመው ወንጀልና የሰብአዊ  መብት ጥሰት አንድን ሀገር እመራላሁ በሚል ይፈጸማል ተብሎ የማይገመትና አሳፋሪ ወንጀል ነው።   በተወሰኑ የተደራጁ ቡድኖች የተፈጸመው ዝርፊያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለትውልዱ አስተማሪና በታሪክ ሊደገም የማይገበው ነው፡፡ ወንጀሉን የፈጸሙት አካላትን ለህግ በማቅረብ  የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ የጠቆመው ወጣቱ  ተጠርጣሪዎችን ለህግ አሳልፎ  በመስጠት በኩል የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል። "በደሀ ህዝብ ሀብትና ንብረት ላይ ይህን ያህል አይን ያወጣ ወንጀል ሲፈጸም መንግስት  ማስቆም አለመቻሉ ያሳዝናል" ያለው ደግሞ ወጣት ደምስ እሸቱ ነው። የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በወንጀሉ የተሳተፉ አካላት የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የኢትዮጵያ ህዝብን መካስ እንደሚገባ ወጣቱ ተናግሯል፡፡ መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰበው ወጣቱ  ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በማጋለጥ በኩል የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም