ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና የታላቁ ሩጫ ውድድር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል-የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ ህዳር 4/2011 የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ። ኮሚሽኑ አያይዞም በርካታ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድርም በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም ነው ያስታወቀው። ህዳር 8 እና 9 ቀን 2011 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በተመሳሳይ በየዓመቱ የሚካሄደውና በርካታ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድርም እንደሚካሄድ ይታወቃል። በዚህም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የጸጥታ ኮማንድ ፖስት ተዋቅሮ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መግባቱን ምክትል ኮሚሽነሩ ዘላለም መንግስቴ ተናግረዋል። ለፖሊስ አመራሮችና አባላትም አስፈላጊ ገለጻና አቅጣጫ መሰጠቱንም አብራርተዋል። ኮሚሽነሩ ባለፈው ሳምንት የኢትዮ-ኤርትራና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የቤተሰብ ሩጫ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት መካሄዱን አውስተዋል። በዚህም ጉባኤውም ሆነ የሩጫ ውድድሩ የአገሪቱን ብሎም የከተማዋን መልካም ገጽታ የሚገነባ በመሆኑ ህብረተሰቡ ለጸጥታው ስራ የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል። ህብረተሰቡ የተለየ ነገር ሲያጋጥመውም በስልክ መስመር 011-1-26-43-77፣ 011-1-26-43-59፣ 011-1-11-01-11 እንዲሁም በነጻ የስልክ መስመር 991 እና 918 በመጠቀም ጥቆማ ማድረግ እንደሚችልም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም