ክሊኒኩ ለ5ሺህ 762 ሰዎች ነፃ የዓይን ህክምና አገልግሎት ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ክሊኒኩ ለ5ሺህ 762 ሰዎች ነፃ የዓይን ህክምና አገልግሎት ሰጠ
ነቀምቴ/ሰመራ ህዳር 4/2011 የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ማዕከላዊ ሶኖዶስ ነቀምቴ ቅርንጫፍ የዓይን ኪሊኒክ ለ5ሺህ 762 የአካባቢው ነዋሪዎች ነፃ የዓይን ህክምና አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ ። የቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ደግሞ ከ8ሺ በላይ ሰዎች ነጻ ዓይን ህክምና ለመስጠት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ማዕከላዊ ሶኖዶስ ነቀምቴ ቅርንጫፍ የዓይን ኪሊኒክ አገልግሎቱን የሰጠው ከጋሮማ ልማት ማህበርና ከስዊዝላንድ የዓይን ሐኪሞች ቡድን ጋር በመተባበር ነው። ነጻ የዓይን ህክምና አገልግሎቱ የተሰጠው ከጥቅምት 17/2011ዓ.ም ጀምሮ ለ16 ቀናት መሆኑን የክልኒኩ ዳይሬክተር አቶ ተሰማ ጃለታ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ አገልግሎቱም የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ፣ የዓይን ምርመራና ህክምና ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል። የጋሮማ ልማት ማህበር ኃላፊ ቄስ ዶክተር ዓለሙ ነጋ በበኩላቸው ማህበሩ የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት ከስዊዝላንድ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ሶስት ሀኪሞች በመጋበዝ ከአካባቢው ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ሐኪሞቹ በቀጣይነትም በደንቢዶሎ፣ ጊምቢ፣ ነጆ፣ ሻምቡ፣ ጊዳ አያናና አምቦ ተመሳሳይ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡ ከታካሚዎቹ መካከል የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት ትዕግስት ሾኔ ለተደረገላቸው የህክምና ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ ሌላው ታካሚ አቶ ቀነዓ ድንሳ በሰጡት አስተያየት ለረጅም ዓመታት ያስቸግራቸው የነበረው የዓይን ሞራ ግርዶሽ በቀዶ ህክምና እንደተወገደላቸው ተናግረዋል። ከፍለው ለመታከም አቅም በማታጣታቸው አጥተውት የነበረው ብርሃን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ዘንደሮ ከ8ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ነጻ የዓይን ህክምና ለመስጠት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡ የሆስፒታሉ የዓይን ሃኪሞች ቡድን መሪ ዶክተር ግሩም ወልደገብርኤል እንዳሉት አገልግሎቱን ለመስጠት እየሰሩ ያሉት በኦሮሚያ ፍቼ ፣ በደቡብ ወራቤ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ነው፡፡ በአፋር ክልል ከዱብቲ ሆስፒታል ጋር መተባበር ሰሞኑን ከ2ሺ በላይ ሰዎች ተቃጠሚ ያደረገ ነጻ የዓይን ህክምና አገልግሎት መስጠታቸውን አመልክተዋል፡፡