ቀጥታ፡

በከተማዋ የሚደርሱ አደጋዎችን በፍጥነት ለመቆጣጠር ባለስልጣኑ በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ ህዳር 4/2011 በአዲስ አበባ ከተማ ድንገተኛ አደጋዎች ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትሉ በፍጥነት ለመቆጣጠር የከተማዋ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ። ባለስልጣኑ በበኩሉ አደጋዎችን በፍጥነት ለመቆጣጠር እንቅፋት የሆነብኝ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት የላላ መሆኑ ነው ብሏል። ባለስልጣኑ የአደጋ ስጋት ለመቀነስ ያለመ ውይይትና የ2011 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ አመት አፈፃፀሙን አስመልክቶ ከህዝብ ክንፉ ጋር ውይይት አድርጓል። በተጠናቀቀው የሩብ ዓመትም 59 የእሳት አደጋዎች በከተማዋ የደረሱ ሲሆን በ2010 ተመሳሳይ ወቅት ከደረሱ 51 አደጋዎች ቁጥር አንጻር ከፍ ያለ አደጋ ማጋጠሙን አውስቷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በዚሁ ወቅት እንዳሉት የባለስልጣኑ ሰራተኞች የእሳት አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ነው ወደቦታው የሚደርሱት በማለት ባለስልጣኑ ፍጥነት እንደሚጎድለው ያወሳሉ። ከተሳታፊዎቹ መካከል ሻምበል ጥላሁን ትርፌሳ እንዳስረዱት የባለስልጣኑ ሰራተኞች አደጋው ንብረት ካወደመና ህይወት ካሳለፈ በኋላ ዘግይተው ነው ወደቦታው የሚደርሱት ብለዋል። ከደረሱም በኋላ በፍጥነት እሳቱን በመቆጣጠር ጉዳቱን ለመቀነስ እየሰሩ አይደሉም ነው የሚሉት። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ጌታቸው በበኩላቸው ባለስልጣኑ ምጥ ለያዛቸው እናቶችና ለታማሚዎች የአምቡላንስ አገልግሎት እየሰጠ ቢገኝም አደጋ የደረሰበት ቦታ ላይ በፍጥነት ከመድረስና ከመቆጣጠር አንፃር ክፍተት አለበት ብለዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ ባለስልጣኑ በፍጥነት አደጋውን ለመቆጣጠርም ችግር የሚሆኑትን የመንገድ መሰረተ ልማትና የኤሌክትሪክ ኃይል ችግርን ለመመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባም ነው ያስረዱት። የመንገዶች መዘጋጋትና ምቹ አለመሆን እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት አለመኖር ባለስልጣኑ አደጋዎችን በፍጥነት ለመቆጣጠር እንዳይችል ማድረጉን የገለፁት ደግሞ  የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የቅድመ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቤቶ ዲማ ናቸው። አደጋዎች ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱት ከቅንጅት መላላት በተጨማሪ ኀብረተሰቡ በፍጥነት ለባለስልጣኑ መረጃ ባለማድረሱ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል። በቀጣይ የከተማ አቀፍ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር እቅድ ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር አደጋን ለመከላከልና አደጋ ከደረሰ በኋላ ሊደረጉ የሚገባቸው ስራዎች ላይ ውይይት በማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል። አቶ ቤቶ አደጋን ቀድሞ ለከመላከልም የተጀመሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለፁት። የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን በከተማዋ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  እንዲሁም የቅድመ ሆስፒታል አምቡላንስና አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ስምንት ቅርንጫፎች አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም