የመቀሌ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል ከንቲባ ሾመ - ኢዜአ አማርኛ
የመቀሌ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል ከንቲባ ሾመ
መቀሌ ጥቅምት 4/2011 የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ኢንጅነር አርአያ ግርማይ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሸመ። ተሿሚው ቀደም ሲል የከተማው አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት ወደ ሌላ የስራ ኃላፊትን በመሄዳቸው እሳቸው ተክተው እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡ ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ኢንጂነር አርአያ ግርማይ የከንቲባ ስራና ኃላፊነት እንዲሰሩ በሙሉ ድምጽ መርጧቸዋል፡፡ ኢንጅነሩ ካላቸው የትምህርት ዝግጅት ሌላ ለረጅም ዓመታት የሱር ኮንስትራክሽን ኃለፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የፕሮጀክት አስኪያጅና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆኖው አገልግለዋል፡፡ ኢንጅነር አርአያ ግርማይ በበኩላቸው "በእኔ ላይ እምነት የጣለው የከተማው ምክር ቤትና ህዝብ በሙሉ ልብ ሌትና ቀን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል፡፡ አንድ ሰው ብቻውን የከተማውን ልማት መቀየር እንደማይቻል ያመለከቱት ኢንጅነሩ በየደረጃው የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የከተማው አስተዳደር ለዓመታት መፍትሄ ሳያገኝ የቆየውን የመብራትና ውሃ ችግር ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የሲቪል ኢንጅነሪንግ ተማሪ ሃይለየሱስ ግርማይ በሰጠው አስተያየት ተሿሚውን በቅርበት እንደሚያውቃቸው ገልጾ " በአመራር፣ በሙያ ብቃት ያላቸው በመሆኑ መሾማቸው ለከተማው እድገት መፋጠን ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል" ብለዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ አቶ ፍትዊ ባህታ በበኩላቸው ኢንጅነር አርአያ ግርማይ መመረጥ በከተማው ምላሽ ያላገኙ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡