ቀጥታ፡

የሴት ሚኒስትሮች ሹመት ሰላምንና የጾታ እኩልነንት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ምሁራን ገለጹ

መቀሌ ህዳር 4/2011 ኢትዮጵያ በመንግሥት ሥራ አስፈጻሚው አካል ውስጥ 50 በመቶ ሴቶችን በሚኒስትርነት መሾሟ ለአስተማማኝ ሰላምና ለጾታ እኩልነት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ሴት ምሁራን አስታወቁ። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የሴት ምሁራን ኮንፈረንስ አስተናግዷል። ከኢዜአ ሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ፣የኬንያና የኢንዶኔዥያ ሴት ከፍተኛ ምሁራን እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ የሚደነቅና ለሌሎች አገሮች በአብነት የሚጠቀስ ነው። ኬንያቷዋ ዶክተር ናኦሚ ሉሙቴንጋ የምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሃብት አገልግሎት ተቋም መስራችና ዳይሬክተር ናቸው። የመንግሥትን ሥራ አስፈጻሚ አካል በከፊል ለሴት ምሁራን በተለይም በሌሎች አገሮች ባልተለመደ ሁኔታ የአገሪቱን ፕሬዚዳንትና የመከላከያ ሚኒስትርነትን ለሴቶች መሰጠቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል። ሹመቱ ከዚህ በላይም በአገሪቱ ውስጥ ለአስተማማኝ ሰላም መስፈንና የጾታ እኩልነት መረጋገጥ ልዩ ሥፍራ እንደሚሰጣቸው እምነታቸውን ገልጸዋል። ሴቶች ለከፍተኛ የአመራር ሰጪነት ቦታ እንዲበቁና በሳይንሱ ዘርፍ የላቀ ውጤት እንዲበቁ ሌሎችን ከመውቀስ ይልቅ ራሳቸውን በሚገባ ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው ኮንፈረንስ ሴቶችን ለላቀ ብቃት በማዘጋጀት የውሳኔ ሰጪነት ብቃታቸውን ለማሳደግ እንደሚያስችላቸው ዶክተር ናኦሚ ተናግረዋል። ከኢንዶኔዥያ የመጡት ዶክተር ሩሲያን ፍራንሲስኮ ኢምቦ  በበኩላቸው በአፍሪካ  የመጀመሪያቸው በሆነው ጉብኝታቸው  የተፈጠረባቸውን ስሜትና  ሴቶችን ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ቦታ እንዲይዙ ማድረግ በኔ እምነት ለሴቶች የተሰጠ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡ ‘‘ሳይንስን መሰረት ያላደረገ ቢዝነስ፣ፈጠራም ሆነ አመራር ውጤታማ ሊሆን አይችልም ” ያሉት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንትና  የኮንፈረንሱ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ፈትየን አባይ ናቸው፡፡ “ኢትዮጰያ ውስጥ በከፍተኛ የአመራር ደረጃ የሴቶች ተሳትፎ አምና ስድስት በመቶ ብቻ ነበር” ያሉት ፕሮፌሰሯ፣ከዚህ በፊት ሲቀርብ የነበረው ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ካቢኔው 50 በመቶ በሴት ምሁራን መያዙን ተናግረዋል። ኮንፈረንሱ የአመራር ሰጪነትን ቦታው ወደ ሴት ወጣት ምሁራን ለማሸጋገር አጋዥ መሆኑንና ወጣት ሴቶችም የሚደርስባቸውን ፈተናዎች በጽናት በመጋፈጥ ለላቀ ውጤት መትጋት ይገባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም