ኮሚሽኑ የአፍሪካን ሴቶች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጎልበት ድጋፍ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ የአፍሪካን ሴቶች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጎልበት ድጋፍ ያደርጋል
አዲስ አበባ ህዳር 4/2011 የአፍሪካን ሴቶች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጎልበት ድጋፍ እንደሚደረግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ቬራ ሶንግዌ ገለጹ። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኮሚሽኑን ዋና ጸሀፊ ቬራ ሶንግዌን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ዋና ጸሀፊዋ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጎልበት የምታደርገውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል። በኢትዮጵያ የተጀመረው የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ልምዱ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም እንዲስፋፋ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ኮሚሽኑ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጎልበት የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲሁም የቴክኒክና የማማከር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው የሴቶችን የመሪነት ብቃት ለማሳደግና አቅም ለማጎልበት ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዚዳንቷ ፅህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ለአገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና እድገት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን አውስተዋል። ከዚህ ባለፈም በመንግስታቱ ድርጅት የተለያዩ ተቋማት በተለይም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በሚደረጉ የማሻሻያ ስራዎች ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ገልጸዋል።