በመንግሥት የሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶችን አስተዳደርና አመራር ሥርዓት ለማስያዝ የሚያስችል ህግ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመንግሥት የሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶችን አስተዳደርና አመራር ሥርዓት ለማስያዝ የሚያስችል ህግ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ ህዳር 4/2011 በመንግስት የሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶችን አስተዳደርና አመራር ሥርዓት ለማስያዝ የሚያስችል ህግ እየተረቀቀ እንደሆነ የፕላን ኮሚሽን ገለፀ። የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ የተለያዩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል። በተለይ በአሁኑ ወቅት የስኳር፣ ኃይል ማመንጫ፣ መስኖንና መንገድን ጨምሮ በአገር ኃብትና ብድር ጭምር ግንባታቸው እየተካሄዱ ያሉት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ አይታይም። ይህም አገሪቱን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋት ከመሆኑም በላይ ምጣኔ ኃብታዊ እድገቱም በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይጓዝ ድርሻ ያለው መሆኑን የመስኩ ምሁራን ይገልፃሉ። የፕሮጀክቶች መዘግየት መንግስት ለዜጎች የልማት ፍላጎት በተገቢው ጊዜ ምላሽ ለመስጠት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዳይወጣም እያደረገው መሆኑም አንደዚሁ። የአብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ወጪ የሚሸፈነው በብደር መሆኑ ደግሞ የአገሪቱን ዕዳ ጫና የከፋ እንደሚያደርገውም ይነገራል። በመሆኑም እነዚህን መሰረታዊ የምጣኔ ኃብት ፈተናዎች በማለፍ ግልፅ የሆነ ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን ማእከል ያደረገ፤ ውጤታማ የፕሮጀክት አፈጻፀም ለማምጣት የሚያግዙ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ነው የፕላን ኮሚሽን ያስታወቀው። የኮሞሽኑ የልማት ፕሮጀክቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በረከት ፍሰሃጽዮን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቶች ከውጥናቸው ጀምሮ እስከትግበራቸው ድረስ ያለውን ሂደት የሚመራ ህግና ዘመናዊ አሰራር ይዘረጋል። "በዚህም መሰረት ፕሮጀክቶች የሚዘጋጁበት፣ የሚገመገሙበት፣ የሚመረጡበት፣ በትግበራ ሂደትና ከትግበራ በኋላም አገልግሎት ወደመስጠት የሚሸጋገሩበትን ሂደት በአግባቡ ለመምራትና ለማስተዳደር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው" ብለዋል። የህግ ማዕቀፉ በመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ላይ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችል ሲሆን ይህንንም ለማስፈጸም የሚስችሉ ስድስት መመሪያዎች ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። የህግ ማዕቀፉ ተግባራዊ ሲደረግም በመንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር ስርአት ውስጥ የተለያዩ አካላት ስልጣንና ኃላፊነት፣ ሁሉም አካላት ሊከተሏቸው የሚገቡ መርሆዎችና አሰራሮች ምን መሆን አለባቸው የሚል ግልጽ የሆነ አሰራር ስላልነበረ ያንን ለመፍታትም ያስችላል። እናም ህጉ ፕሮጀክቶች የሚመረጡበት፣ የሚዘጋጁበት፣ የሚቀርቡበት፣ የሚገመገሙበት፣ ክትትል የሚደረግባቸውና ሲጠናቀቁም አገልግሎት የሚሰጡበትን ግልጽ አሰራር ይቀይሳል ነው ያሉት። ህግ የማርቀቅ ሥራው ኮሚሽኑ በመጪዎቹ በመቶ ቀናት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከሚያከናወናቸው ተግባራት መካከል አንዱ ሲሆን ሁነኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎም ታምኖበታል።