የአሜሪካ መንግስት የአምስት ዓመት የከተማ ጤና ማጠናከሪያ መርኃ ግብር ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካ መንግስት የአምስት ዓመት የከተማ ጤና ማጠናከሪያ መርኃ ግብር ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ህዳር 4/2011 በአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤድ) ለአምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ሲተገበር የቆየው ብሔራዊ የከተማ ጤና አጠባበቅ መርኃ ግብር መጠናቀቁ ይፋ ሆነ። በጠቅላላው 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል የተባለው መርሃ ግብሩ የተሳካ እንደነበር የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል። መርኃ ግብሩ አዲስ አበባን ጨምሮ 50 በሚጠጉ የክልል ከተሞች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ቤተሰቦች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ አደርጓል። ጎን ለጎንም መርሃ ግብሩ 2 ሺህ 500 በከተማ ጤና አገልግሎት የተሰማሩ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ሥልጠና በመስጠት አገልግሎቱ እንዲጠናከር አግዟል። መርሃ ግብሩ በዋነኝነት የከተማ ነዋሪዎች የንጹህ ውኃና የጽዳት አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል ነው የተባለው። በኢትዮጵያ የተራድኦው ዳይሬክተር ሌስሌ ሪድ እንደተናገሩት፤ "የትኛውም አገር ያለ መሠራታዊ ጤና ተደራሽነት ሁሉን አቀፍ እድገትን ሊያሳካ አይችልም"፡፡ በዚህ ረገድ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ ለውጥ እንድታመጣ በዘርፉ ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና ኤክስቴንሽንና የመሠረታዊ ጤና ክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ተመስገን አየሁ ድርጅቱ ባለፉት አምስት ዓመታት የተገበረው የጤና ልማት መርሃ ገብር ድጋፍ የተሳካ እንደሆነ ተናግረዋል። "ድርጅቱ ለጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ሥልጠና ሰጥቷል፣ የሥራ መተግበሪያ መመሪያዎችን አዘጋጅቷል፤ እንዳስፈላጊነቱም መመሪያዎቹን ከልሷል" ብለዋል። በተጓዳኝም በከተሞች ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው ይህም የጤና አገልግሎት አሰጣጡን እንዳሻሻለው አረጋገጠዋል። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲክስ ኤጀንሲ ባለፈው ዓመት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከጠቅላላ የአገሪቱ ሕዝብ 20 በመቶ የሚሆነው የሚኖረው በከተማ አከባቢ ነው። ኤጀንሲው ባስቀመጠው ደረጃ መሰረት፤ ከተማ የሚባለው ከ2000 በላይ ነዋሪ ያላቸውና ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከግብርና ውጪ ሥራ ዘርፍ የተሰማራ ነው። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ2001 ዓ.ም በከተሞች ያለውን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን መርኃ ግብር መተግበር መጀመሩ የሚታወስ ነው። የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞቹ በነርሲንግ ዲፕሎማ ወይም 10ኛ ክፍልን ያጠናቀቁና ሶስት ዓመት በመስኩ ሥልጠና የወሰዱ ናቸወ። ይህም የጤና ኤክስቴንሽን መርኃ ግብር በዋናነት ከከተማ መስፋፋት ጋር ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ የተጀመረ የጤና ሥርዓት ነው። የኤክስቴንሽን መርሃ ገብሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። እነዚህንም አገልግሎቶች ወደ ኅብረተሰቡ የሚያደርሱ 500 የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ሲሆኑ ለ400 ከተሞች አገልግሎቱን ያደርሳሉ። አንድ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኛ በአማካይ 500 ለሚሆኑ ቤተሰቦች የቤት ለቤት አገልግሎት ትሰጣለች።