በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የቱርክ ኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ ከአራት ወር በኋላ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የቱርክ ኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ ከአራት ወር በኋላ ይጀመራል
አዲስ አበባ ህዳር 4/2011 በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በ750 ሚሊዮን ዩሮ መዋእለ ንዋይ የሚመሰረተውን የቱርክ ኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ ከአራት ወር በኋላ ለማስጀመር በትኩረት እየተሰራ ነው ተባለ። የኢንዱስትሪ ዞኑን ለመገንባት ስምምነት የፈጸመው የቱርክ ኩባንያ (Turkish Industry Holding) ሊቀመንበር መህመት ኮስኩን በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግርማ ተመስገን ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ነው ይህ የተነገረው። በውይይቱ ወቅት የኩባንያው ሊቀመንበር መህመት ኩስኩን ኩባንያቸው የግንባታ ሂደቱን ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጸህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ግንባታው ከአራት ወር በኋላ ይጀመራል ያሉት ሊቀመንበሩ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታም በሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር ገልጸዋል። የቱርኩ ኢንደስትሪ ሆልዲንግ ኩባንያ ሊቀመንበር መህመት ኮስኩንና የስራ ባልደረቦቻቸው በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም ባደረጉት ጉብኝት ኩባንያው በሃይል ማመንጫ ዘርፍ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ከውሃና መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጋር ባደረጉት ውይይት መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ቱርክ በኢትዮጵያ የምትገነባው ኢንዱስትሪ ዞን እ.አ.አ በ2005 አገሪቷ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት የማጠናከር ስራ አካል ነው። በሌላ በኩል ትሪኒዳድና ቶቤጎ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች። የትሪኒዳድና ቶቤጎ ሪፑብሊክ ፕሬዝዳንት ፓውላ ሜእ ዊክስ በአገራቸውና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልጉ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገልጿል። ፕሬዝዳንቷ ሰሞኑን በአገራቸው ተቀማጭና ተወካይ ለሆኑ አምባሳደሮች ያደረጉትን አመታዊ ብሄራዊ ግብዣ ተከትሎ በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደዋኖ ከድር ጋር ባደረጉት ውይይት መንግስታቸው ከአገራችን ጋር ያለውን አጠቃላይ ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናገረዋል። አምባሳደር ደዋኖ በበኩላቸው ከአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኒስ ሞሰስ ጋርም የሁለቱን አገሮች አጠቃላይ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ተወያይተዋል። በትሪኒዳድና ቶቤጎ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ጋርም ተገናኝተው ስለ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል። በኩባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በውክልና ከሚሸፍናቸው አገሮች መካከል ትሪኒዳድና ቶቤጎ ትገኝበታለች።