የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ ተቸግረናል፤-የቀብሪ ደሃር ከተማ ነዋሪዎች

77
ጅግጅጋ ህዳር 4/2011 በሶማሌ ክልል የቀብሪደሃር ከተማ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ መቸገራቸውን ገለጹ፡፡ የቆራሄ ዞን አስተዳደር የአገልግሎቱ መቋረጥ በሥራ ፈጠራ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ይላል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተማዋን የ24 ሰዓት አገልግሎት ተጠቃሚ  ለማድረግ ሥራ መጀመሩን ገልጿል ፡፡ ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳመለከቱት በከተማዋ ከሦስት ወራት በላይ የተቋረጠው አገልግሎት በሥራቸውና በኑሮአቸው ላይ ችግር ፈጥሮባቸዋል። በከተማዋ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ፈይሰል መሐመድ የአገልግሎቱ መስተጓጎል ሥራቸውን እንደጎዳባቸው ይናገራሉ፡፡ በተለይም  ከከተማዋ ሞቃታማ  የአየር ጸባይ ጋር ተያይዞ ምግብን በማቀዝቀዣ አቆይቶ ለመጠቀም እንደተቸገሩ ገልጸዋል፡፡ የቀበሌ 03 ነዋሪው አቶ አህመድ ሰይድ በፈረቃ ታገኝ የነበረው አገልግሎት ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ከምሽት 12 እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ብቻ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው አገልግሎት በመቋረጡ ጨለማ ውስጥ ለመኖር ተገደዋል። የቆራሄ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱራህማን አህመድ ለከተማዋ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ጄኔሬተር በመበላሸቱ ችግሩ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግሩን እንዲፈታ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢያሳውቁም፤ ምላሽ አልሰጠንም ይላሉ፡፡ በከተማዋ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንድትሆን የአስተዳደሩ ጥያቄና ፍላጎት መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡ "የመብራት አገልግሎት ቢኖር ወጣቶች ለስላሳና ውሃ አቀዝቅዞ በመሸጥ ገቢ እንዲያገኙ  የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል" ሲሉ አገልግሎቱ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች  በመቋረጡ ለተጨማሪ ወጪ ና "ተቋማቱ ለሕዝብ የሚሰጡት አገልግሎት እንዲስተጓጉል አድርጓል" ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሶማሌ ክልልሥራ አስፈጻሚ አቶ አንተነህ መላኩ እንደተናገሩት በከተማዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቆረጠው በቀን ለስድስት ሰአት አገልግሎት የሚሰጠው ዋናው ጄኔሬተር በመበላሸቱ  ነው ብለዋል ፡፡ ጄኔሬተሩ ያጋጠመውን ብልሽት ከጥገና ሠራተኞች አቅም በላይ በመሆኑ ከአዲስ አበባ በሚመጡ ባለሙያዎች ጥገና ተከናውኖለት በዚህ ሳምንት ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ከተማዋ የ24 ሰዓት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ  እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ነዋሪዎችና የአስተዳደር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ሥራ አስፈፃሚው ጠይቀዋል፡፡ ቀብሪ ደሃር ከ100 ሺህ ህዝብ በላይ የሚኖሩባት ከተማ ስትሆን፣አንድ ዩኒቨርሲቲ፣ አራት ኮሌጆች፣ ሁለት ሆስፒታሎች፣ አየር ማረፊያ፣ ሆቴሎች፣ የንግድ ድርጅቶች፣መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አሏት፡፡ ከተቆረቆረች ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው ከተማ መሆኑን ለአካባቢው መሪዎች መቀመጫና የሥልጣኔ ምንጭ ሆና መቆየቷን መረጃዎች ያመለክታሉ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም