ቀጥታ፡

የዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን ለ41 ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የአሰልጣኝነት ፈቃድ ሰጠ

አዲስ አበባ ህዳር 3/2011 የዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን ለ41 ኢትዮጵያውያን የቼስ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የቼስ አሰልጣኝነት ፈቃድ ሰጠ። ግሪካዊው የቼስ ግራንድ ማስተር ኢፍስትራቲዮስ ግሪቫስ በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ለኢትዮጵያን አሰልጣኞች ስልጠና እና ስልጠናውንም ተከትሎ ባለፈው ዓለም አቀፍ ፈቃድ ለሰልጣኞች ፈተና መስጠቱ የሚታወስ ነው። ዓለም አቀፍ የቼስ አሰልጣኝ ግሪቫስ የሰልጣኞቹን የፈተና ውጤት ለዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ማቅረቡም ይታወቃል። በዚሁ መሰረት የቼስ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ የፈተናውን ውጤት በመገምገምና ባስቀመጣቸው መስፈርቶች መሰረት ለ41 ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የቼስ አሰልጣኝነት(Instructor) ፈቃድ መስጠቱን የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ ገልጸዋል። የአሰልጣኝነት ፈቃዱ የቼስ ስፖርትን ማስፋፋትና ማስተማር፣ በብሔራዊ ደረጃ ብቁ የሚባሉ የቼስ ተጫዋቾችን ማሰልጠንና መመልመልና ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን መስጠት በሚል ሶስት ዘርፍ የተከፋፈለ እንደሆነም ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ ፈቃድ እንዳለው ያስታወሱት አቶ ሰይፈ፤ ይህም የዓለም አቀፍ የአሰልጣኝነት ፈቃድ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ 42 እንደሚያሳድገው አመልክተዋል። የቼስ ባለሙያዎቹ የተወጣጡት በየክልሎቹ ካሉ የስፖርቱ ባለሙያዎችና ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የተወጣጡ መምህራን እንደሆነም አስረድተዋል። የቼስ ስፖርትን ማስፋፋትና ማስተማር ዘርፍ ፈቃድ ካገኙት ደጀኔ ዘላለም ከአሰልጣኝነቱ በተጨማሪ በዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ የዳኝነት ፈቃድ እንዳለውም አንስተዋል። ስፖርቱን በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ለማስተዋወቅና ብቁ የቼስ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት አኳያ የቼስ ባለሙያዎቹ ፈቃድ ማግኘታቸው ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል። ለዓለም አቀፍ የቼስ አሰልጣኝነት የሚሆኑ ሰልጣኞችን በመልመል የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ላላፉት ሶስት ዓመታት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርም ነው አቶ ሰይፈ ያስረዱት። ቼስ በቤት ውስጥ ከሚካሄዱ የስፖርት ዓይነቶች አንዱ ሲሆን፤ የሰው ልጅ አእምሮን የሚያሰፋ በመሆኑ በዓለም ላይ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ያዘወትሩታል። ኢትዮጵያ እና የቼስ ስፖርት የረጅም ዓመት ቁርኝት እንዳላቸው ይነገራል። ቼስ ስፖርት ከአንድ ሺ ዓመት በፊት «ሰንጠረዥ» በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ውስጥ ይዘወተር እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም